የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 1:26-45

የሉቃስ ወንጌል 1:26-45 አማ05

ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በገሊላ ምድር ወደምትገኝ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ከእግዚአብሔር ተላከ። የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ወደ እርስዋ መጥቶ፦ “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ [አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ]” አላት። እርስዋም በመልአኩ አነጋገር በጣም ደንግጣ፥ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ! ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። በእስራኤልም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፤ ታዲያ፥ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአብሔርም ኀይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ሕፃን ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ይባላል። ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳ መኻን ስትባል ኖራ አሁን በስተእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ ከፀነሰችም እነሆ፥ ስድስተኛ ወርዋ ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።” ከዚያም በኋላ ማርያም፥ “እነሆ! እኔ የጌታ አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ መልአኩ ተለይቶአት ሄደ። በዚያን ጊዜ ማርያም በተራራማው በይሁዳ አገር ወዳለችው ከተማ በፍጥነት ተነሥታ ሄደች። ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥ የማርያምን የሰላምታ ቃል በሰማች ጊዜ በማሕፀንዋ የነበረው ሕፃን ዘለለ። ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ ከአንቺ የሚወለደውም የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ልትጐበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው፤ ገና የሰላምታሽን ድምፅ ከመስማቴ በማሕፀኔ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። አንቺ ጌታ የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የተባረክሽ ነሽ!”

Free Reading Plans and Devotionals related to የሉቃስ ወንጌል 1:26-45