በእኛ ዘንድ የተፈጸመውንና የታመነውን የሥራውን ዜና በሥርዐት ሊጽፉ የጀመሩ ብዙዎች ናቸው። ከእኛ አስቀድሞ በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩ እንደ አስተላለፉልን፤ የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው ተከትዬ፥ ሁሉንም በየተራው እውነተኛውን እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሁኖ ታየኝ። የተማርኸውን የነገሩን እውነት ጠንቅቀህ ታውቅ ዘንድ። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ሥርዐትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ። ልጅም አልነበራቸውም፤ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፤ ሁለቱም አርጅተው ነበር፤ ዘመናቸውም አልፎ ነበር። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራው የክህነትን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥ ካህናት እንደሚያደርጉት የሚያጥንበት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸልዩ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክም በዕጣን መሠውያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሀትም ረዓድም ወረደበት። መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል። ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል። እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኀይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም የእግዚአብሔርን መልአክ እንዲህ አለው፥ “ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅችአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል።” መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ። አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል።” ሕዝቡ ግን ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ዘግይቶ ነበርና እጅግ ተደነቁ። ወደ እነርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነርሱን ማነጋገር ተሳነው፤ በቤተ መቅደስም የተገለጠለት እንዳለ ዐወቁ፤ እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከታቸው ኖረ። ከዚህም በኋላ የማገልገሉ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ። ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ፅንስዋንም ለአምስት ወር ሸሸገች፤ እንዲህ ስትል፦ “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጐበኘኝ ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ።” በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሟ ናዝሬት ወደምትባለው ወደ አንዲት የገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሚሆን ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨችው ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፤ የዚያችም ድንግል ስምዋ ማርያም ይባል ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፥ “ደስ ያለሽ፥ ጸጋንም የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። እርስዋም በአየችው ጊዜ ከአነጋገሩ የተነሣ ደነገጠችና “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ ዐሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፥ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፥ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፥ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። እነሆ፥ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን ኤልሣቤጥም እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”። ማርያምም መልአኩን፥ “እነሆኝ፥ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለችው፤ ከዚህ በኋላም መልአኩ ከእርስዋ ዘንድ ሄደ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos