የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን፦ እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ። የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos