እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ አግድማችሁም ብትሄዱብኝ፥ እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ እንደ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። የኮረብታ መስገጃዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በእጅ የተሠሩ የዕንጨት ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፤ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፤ የመሥዋዕታችሁንም መዓዛ አላሸትትም። ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም ከእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ በሄዳችሁበትም ሁሉ ሰይፍ ታጠፋችኋለች፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፤ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ። “በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ደስ ይላታል፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፤ ስንበትንም በማድረግዋ ደስ ይላታል። እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። በአሕዛብም መካከል ትጠፋላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። ከእናንተም ተለይተው የቀሩት ስለ ኀጢአታቸው ይጠፋሉ፤ በአባቶቻቸውም ኀጢአት ደግሞ በጠላቶቻቸው ምድር ይቀልጣሉ። “እንደ ከዱኝ፥ ቸልም እንዳሉኝ፥ በፊቴም አግድመው እንደ ሄዱ፥ ኀጢአታቸውንና፥ የአባቶቻቸውን ኀጢአት ይናዘዛሉ። እኔም ደግሞ አግድሜ ከእነርሱ ጋር በቍጣ ሄድሁ፤ በጠላቶቻቸውም ምድር አጠፋቸዋለሁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ያፍራል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይናዘዛሉ፤ ያን ጊዜ እኔ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞም ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን፥ ከአብርሃምም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ዕረፍት ታደርጋለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዐቴን ስለ ተጸየፈች የኀጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም፤ አልጸየፋቸውምም። እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ከግዞት ቤት እንዳወጣኋቸው የቀድሞ ቃል ኪዳናቸውን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ የሰጣቸው ሥርዐቶችና ፍርዶች፥ ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።
ኦሪት ዘሌዋውያን 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 26:27-46
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች