“ለእናንተ በእጅ የተሠራ ጣዖት አታድርጉ፤ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና። ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ የቀደስኋቸውንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። “በሥርዐቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ፥ ብታደርጉትም፥ ዝናሙን በወቅቱ አዘንማለሁ፤ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፤ የሜዳው ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቈረጥ ይደርሳል፤ የወይኑም መቈረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ የሚያስፈራችሁም የለም፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፤ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፤ መቶውም ዐሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ወደ እናንተም እመለከታለሁ፤ አባዛችኋለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ብዙ ጊዜ የተቀመጠውን፥ የከረመውንም እህል ትበላላችሁ፤ አዲሱንም ታስገቡ ዘንድ የከረመውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ባሪያዎች ከነበራችሁበት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ በግልጽም አወጣኋችሁ። “ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዐቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ሰውነታችሁ ፍርዴን ብትሰለች፥ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሀትን፥ ክሳትንም፥ ዐይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያጠፋ ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሏችሁም ያሸንፉአችኋል። ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኀጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ መቅሠፍትን እጨምራለሁ። የትዕቢታችሁን ስድብ አጠፋለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፤ የዱር ዛፎችም ፍሬያቸውን አይሰጡም። “ከዚያም በኋላ በእንቢተኝነት ብትሄዱብኝ፥ ልትሰሙኝም ባትፈቅዱ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። በእናንተ ላይ ክፉዎች የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ይበሉአችኋል፤ እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፤ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። “እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ አግድማችሁም ብትሄዱ፥ እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እበቀላችኋለሁ። የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሸሻላችሁ፤ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ። በጠላቶቻችሁም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፤ በእህል ረሃብ ባስጨነክኋችሁ ጊዜ ዐሥር ሴቶች እንጀራ በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፤ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም።
ኦሪት ዘሌዋውያን 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 26:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች