ኦሪት ዘሌዋውያን 17
17
ደም መብላት ስለ መከልከሉ
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው- 2“ለአሮንና ለልጆቹ፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር፦ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ እንዲህም አለ፦ 3ከእስራኤል ቤት ከመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው በሬ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ 4ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የተመረጠ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ወይም የድኅነት መሥዋዕት ያደርገው ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ በሌላም ቦታ ቢያርደው፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአልና፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 5ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለድኅነት መሥዋዕት ይሠዉታል። 6ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደሙን ይረጨዋል፤ ስቡንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን ያቃጥለዋል። 7መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሥርዐት ይሁን።”
8ለእነርሱ እንዲህ በላቸው፥ “ከእስራኤል ቤት ከመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
10“ከእስራኤልም ልጆች፥ ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ያንም ሰው ከሕዝቡ ለይች አጠፋዋለሁ። 11የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነው፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። 12ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች፦ ‘ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፤ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም’ አልሁ።
13“ከእስራኤልም ልጆች፥ ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል፤ በአፈርም ይከድነዋል። 14የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና፤ ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች፦ የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው። 15የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የሀገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፤ በውኃም ይታጠባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኀጢአቱን ይሸከማል።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ