ኦሪት ዘሌ​ዋ​ው​ያን 16

16
የስ​ር​የት ቀን
1በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ሌላ እሳ​ትን ስላ​መጡ የሞቱ ሁለቱ የአ​ሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሙሴን ተና​ገ​ረው። 2እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን አለው፥ “እኔ በስ​ር​የቱ መክ​ደኛ ላይ በደ​መ​ናው ውስጥ እታ​ያ​ለ​ሁና እን​ዳ​ይ​ሞት በመ​ጋ​ረ​ጃው ውስጥ በም​ስ​ክሩ ታቦት ላይ ወዳ​ለው ወደ ስር​የቱ መክ​ደኛ ወደ ተቀ​ደ​ሰው ስፍራ ሁል​ጊዜ እን​ዳ​ይ​ገባ ለወ​ን​ድ​ምህ ለአ​ሮን ንገ​ረው። 3እን​ዲሁ አሮን ለኀ​ጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት ከላ​ሞች ወይ​ፈን፥ ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕ​ትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀ​ደ​ሰው ስፍራ ይግባ። 4የተ​ቀ​ደ​ሰ​ው​ንም የተ​ልባ እግር ቀሚስ ይል​በስ፤ የተ​ልባ እግ​ርም ሱሪ በገ​ላው ላይ ይሁን፤ የተ​ልባ እግር መታ​ጠ​ቂያ ይታ​ጠቅ፤ የተ​ልባ እግር አክ​ሊ​ልም በራሱ ላይ ያድ​ርግ፤ እነ​ዚህ የተ​ቀ​ደሱ ልብ​ሶች ናቸው፤ ገላ​ው​ንም በውኃ ታጥቦ ይል​በ​ሳ​ቸው። 5ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ማኅ​በር ለኀ​ጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት ሁለት የፍ​የል ጠቦ​ቶች፥ ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት አንድ አውራ በግ ይው​ሰድ።
6“አሮ​ንም የኀ​ጢ​አ​ቱን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈን ያቀ​ር​ባል፤ ለራ​ሱም፥ ለቤ​ተ​ሰ​ቡም ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል። 7ሁለ​ቱ​ንም የፍ​የል ጠቦ​ቶች ወስዶ በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ አጠ​ገብ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያቆ​ማ​ቸ​ዋል። 8አሮ​ንም በሁ​ለቱ የፍ​የል ጠቦ​ቶች ላይ ዕጣ ይጥ​ል​ባ​ቸ​ዋል፤ አን​ዱን ዕጣ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ ሌላ​ው​ንም ዕጣ ለሚ​ለ​ቀቅ። 9አሮ​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ባ​ሔር ዕጣ የሆ​ነ​በ​ትን ፍየል ያቀ​ር​ባል፤ ስለ ኀጢ​አ​ትም መሥ​ዋ​ዕት ያደ​ር​ገ​ዋል። 10የመ​ለ​ቀ​ቅም ዕጣ የሆ​ነ​በ​ትን ፍየል ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​በት ዘንድ፥ ለመ​ለ​ቀ​ቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰ​ድ​ደው ዘንድ በሕ​ይ​ወቱ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያቆ​መ​ዋል።
11“አሮ​ንም ስለ ራሱ ኀጢ​አት የሚ​ሠ​ዋ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈ​ኑን ያቀ​ር​ባል፤ ለራ​ሱም ለቤ​ተ​ሰ​ቡም ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል፤ ስለ ኀጢ​አቱ የእ​ር​ሱን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈ​ኑን ያር​ዳል። 12በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ከአ​ለው መሠ​ዊያ ላይ የእ​ሳት ፍም አም​ጥቶ ጥና​ውን ይሞ​ላል፤ ከተ​ወ​ቀ​ጠ​ውም ልቅ​ምና ደቃቅ ዕጣን እጁን ሙሉ ይወ​ስ​ዳል፤ ወደ መጋ​ረ​ጃ​ውም ውስጥ ያመ​ጣ​ዋል። 13እን​ዳ​ይ​ሞ​ትም የጢሱ ደመና በም​ስ​ክሩ ታቦት ላይ ያለ​ውን መክ​ደኛ ይሸ​ፍን ዘንድ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ዕጣ​ኑን በእ​ሳቱ ላይ ያደ​ር​ጋል። 14ከወ​ይ​ፈ​ኑም ደም ወስዶ በስ​ር​የቱ መክ​ደኛ ላይ ወደ ምሥ​ራቅ በጣቱ ይረ​ጨ​ዋል፤ ከደ​ሙም በመ​ክ​ደ​ኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረ​ጫል።
15“ስለ ሕዝ​ቡም ኀጢ​አት የሚ​ሠ​ዋ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ፍየል ያር​ዳል፤ ደሙ​ንም ወደ መጋ​ረ​ጃው ውስጥ ያመ​ጣ​ዋል፤ በወ​ይ​ፈ​ኑም ደም እን​ዳ​ደ​ረገ በፍ​የሉ ደም ያደ​ር​ጋል፤ በመ​ክ​ደ​ኛው ላይና በመ​ክ​ደ​ኛው ፊት ይረ​ጨ​ዋል። 16ከእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ርኩ​ስ​ነት፥ ከመ​ተ​ላ​ለ​ፋ​ቸ​ውም፥ ከኀ​ጢ​አ​ታ​ቸ​ውም የተ​ነሣ ለመ​ቅ​ደሱ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ እን​ዲ​ሁም በር​ኩ​ስ​ነ​ታ​ቸው መካ​ከል ከእ​ነ​ርሱ ጋር ለኖ​ረች ለም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ያደ​ር​ጋል። 17እርሱ ለማ​ስ​ተ​ስ​ረይ ወደ መቅ​ደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤ​ተ​ሰ​ቡም፥ ለእ​ስ​ራ​ኤል ጉባኤ ሁሉ አስ​ተ​ስ​ርዮ እስ​ኪ​ወጣ ድረስ በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ውስጥ ማንም አይ​ኖ​ርም። 18በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ወዳ​ለው ወደ መሠ​ዊ​ያው ወጥቶ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ ከወ​ይ​ፈ​ኑም ደም፥ ከፍ​የ​ሉም ደም ወስዶ በመ​ሠ​ዊ​ያው ዙሪያ ያሉ​ትን ቀን​ዶች ያስ​ነ​ካል። 19ከደ​ሙም በእ​ርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረ​ጫል፤ ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ርኩ​ስ​ነት ያነ​ጻ​ዋል፤ ይቀ​ድ​ሰ​ው​ማል።
የሕ​ዝ​ቡን ኀጢ​አት ተሸ​ክሞ ወደ በረሃ ስለ​ሚ​ለ​ቀ​ቀው የፍ​የል ጠቦት
20“ስለ​መ​ቅ​ደሱ፥ስለ ምስ​ክ​ሩም ድን​ኳን፥ ስለ መሠ​ዊ​ያ​ውም ማስ​ተ​ስ​ረ​ያና ስለ ካህ​ና​ትም ማን​ጻት ከፈ​ጸመ በኋላ ደኅ​ነ​ኛ​ውን ፍየል ያቀ​ር​ባል። 21አሮ​ንም ሁለ​ቱን እጆ​ቹን በደ​ኅ​ነ​ኛው ፍየል ራስ ላይ ይጭ​ናል፤ በላ​ዩም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች በደል ሁሉ፥ መተ​ላ​ለ​ፋ​ቸ​ውን ሁሉ፥ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ው​ንም ሁሉ ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል፤ በፍ​የ​ሉም ራስ ላይ ያሸ​ክ​መ​ዋል፤ በተ​ዘ​ጋ​ጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰ​ድ​ደ​ዋል። 22ፍየ​ሉም ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸ​ከ​ማል፤ ፍየ​ሉ​ንም ዛፍ በሌ​ለ​በት በም​ድረ በዳ ውስጥ ይለ​ቅ​ቀ​ዋል።
23“አሮ​ንም ወደ ምስ​ክሩ ድን​ኳን ይገ​ባል፤ ወደ መቅ​ደ​ሱም በገባ ጊዜ የለ​በ​ሰ​ውን የተ​ልባ እግር ልብስ ያወ​ል​ቃል፤ በዚ​ያም ይተ​ወ​ዋል። 24በተ​ቀ​ደ​ሰ​ውም ስፍራ ገላ​ውን በውኃ ይታ​ጠ​ባል፤ ሌላ​ው​ንም ልብስ ለብሶ ይወ​ጣል፤ የእ​ር​ሱ​ንም የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ር​ባል፤ ለካ​ህ​ናቱ እን​ዳ​ስ​ተ​ሰ​ረየ ለራ​ሱም፥ ለሕ​ዝ​ቡም ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል። 25የኀ​ጢ​አ​ቱ​ንም መሥ​ዋ​ዕት ስብ በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ ያቃ​ጥ​ለ​ዋል። 26ለመ​ለ​ቀቅ የሚ​ሆ​ነ​ውን ፍየል የወ​ሰደ ሰው ልብ​ሱን ያጥ​ባል፤ ገላ​ው​ንም በውኃ ይታ​ጠ​ባል፤ ከዚ​ያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገ​ባል። 27ለማ​ስ​ተ​ስ​ረ​ያም እን​ዲ​ሆን ደማ​ቸው ወደ መቅ​ደስ የገ​ባ​ውን የኀ​ጢ​አ​ቱን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈ​ንና የኀ​ጢ​አ​ቱን መሥ​ዋ​ዕት ፍየል ከሰ​ፈሩ ወደ ውጭ ያወ​ጡ​አ​ቸ​ዋል፤ ቍር​በ​ታ​ቸ​ው​ንም፥ ሥጋ​ቸ​ው​ንም፥ ፈር​ሳ​ቸ​ው​ንም በእ​ሳት ያቃ​ጥ​ላሉ። 28ያቃ​ጠ​ላ​ቸ​ውም ሰው ልብ​ሱን ያጥ​ባል፤ ገላ​ው​ንም በውኃ ይታ​ጠ​ባል፤ ከዚ​ያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገ​ባል።
29“ይህም የዘ​ለ​ዓ​ለም ሥር​ዐት ይሁ​ን​ላ​ችሁ። 30በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስ​ተ​ስ​ረያ ይሆ​ን​ላ​ች​ኋ​ልና በሰ​ባ​ተ​ኛው ወር ከወ​ሩም በዐ​ሥ​ረ​ኛው ቀን ራሳ​ች​ሁን አስ​ጨ​ን​ቋት፤ የሀ​ገር ልጅም፥ በእ​ና​ን​ተም መካ​ከል የተ​ቀ​መጠ እን​ግዳ ሥራን ሁሉ አት​ሥ​ሩ​በት፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ከኀ​ጢ​አ​ታ​ችሁ ሁሉ ትነ​ጻ​ላ​ችሁ። 31ታላቅ ሰን​በት ይሆ​ን​ላ​ች​ኋል፤ ራሳ​ች​ሁ​ንም ታዋ​ር​ዳ​ላ​ችሁ፤ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሥር​ዐት ነው። 32የሚ​ቀ​ባ​ውም፥ በአ​ባ​ቱም ፋንታ ካህን ሊሆን የሚ​ካ​ነው ካህን ያስ​ተ​ስ​ርይ፤ የተ​ቀ​ደ​ሰ​ው​ንም የተ​ልባ እግር ልብስ ይል​በስ። 33ለቅ​ድ​ስተ ቅዱ​ሳ​ንም ያስ​ተ​ስ​ርይ፤ ለም​ስ​ክሩ ድን​ኳን፥ ለመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም ያስ​ተ​ስ​ርይ፤ ለካ​ህ​ና​ቱም፥ ለጉ​ባ​ኤ​ውም ሕዝብ ሁሉ ያስ​ተ​ስ​ርይ። 34ይህም አንድ ጊዜ በዓ​መት ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ስለ ኀጢ​አ​ታ​ቸው ሁሉ ያስ​ተ​ሰ​ርይ ዘንድ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሥር​ዐት ይሁ​ን​ላ​ችሁ።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዳ​ዘ​ዘው እን​ዲሁ አደ​ረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ