መጽሐፈ ኩፋሌ 1
1
1የእስራኤል ልጆች ከግብፅ በወጡበት በመጀመሪያው ዘመን እንዲህ ሆነ። በሦስተኛው ወር፥ ያ ወር በባተ በዐሥራ ስድስተኛው ቀን፥ እግዚአብሔር፥ “ከእኔ ዘንድ ወደዚህ ተራራ ውጣ፤ በጻፍኸውም መጠን ልብ ታስደርጋቸው ዘንድ ሕጉና ሥርዐቱ የተጻፉባቸውን ሁለቱን የዕንቍ ጽላት እሰጥሀለሁ” ብሎ ለሙሴ ተናገረ። 2ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። የእግዚአብሔርም ብርሃን በደብረ ሲና ተገለጠ። ስድስት ቀንም ደመና ጋረደው። 3በሰባተኛዪቱም ቀን በደመና መካከል ሆኖ ሙሴን ጠራው፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በተራራው ራስ ላይ እንደ እሳት ሲነድድ አየ።
4ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀመጠ። እግዚአብሔርም ያለፈውንና የሚመጣውን፥ ሕጉ የሚጠበቅበትንና አምልኮቱ የሚነገርበትን፥ የዘመኑን ሁሉ አከፋፈል ነገር አመለከተው። 5እንዲህም አለው፥ “በዚህ ተራራ ላይ እኔ በምነግርህ ነገር ሁሉ ልብህን አኑር። በአንተና በእኔ መካከል በደብረ ሲና ዛሬ ለልጆቻቸው የሚደረገውን፥ እኔ የምሠራውን ሥርዐት ለማስፈረስ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ እንደ ተለየሁአቸው ልጆቻቸው ይሰሙ ዘንድ በመጽሐፍ ጻፈው።” 6ይህ ሁሉ ነገር በእነርሱ ላይ በመጣባቸው ጊዜ እንዲህ ይናገራል። በፈረድሁባቸው ሁሉ፥ በሥራቸውም ሁሉ ከእነርሱ ይልቅ እኔ እውነተኛ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ከእነርሱም ጋር ያለሁ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7አንተም እኔ ዛሬ የነገርሁህን ይህን ሁሉ ነገር ጻፍ። እኔ ቍጣቸውን አውቃለሁና፥ ማርና ወተትን የምታስገኝ ሀገርን ለልጆቻችሁ እሰጣለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደማልሁላቸው ሀገር ሳላገባቸው አንገታቸው ደንዳና እንደ ሆነ አውቃለሁና፥ በልተውና ጠግበው ከመከራቸው ሁሉ ወደማያድናቸው ወደ ልዩ ጣዖት ይመለሳሉና። 8ይህች መጽሐፍ በእነርሱ ላይ ሥርዐት ትሁንባቸው። እኔ የማዝዛቸውን ትእዛዜን ሁሉ ይዘነጋሉና፥ አሕዛብንም ተከትለው ወደ ኀጢአታቸው ይሄዳሉና፥ ለጣዖቶቻቸውም ይገዛሉና፤ በእነርሱም መከራንና ጭንቅን፥ ጦርንም ለማምጣት መሰናክል ይሆንባቸዋል።
9“ብዙ ሰዎች ይጠፋሉ፥ ተይዘውም በጠላቶቻቸው እጅ ይወድቃሉ። ሥርዐቴንና ትእዛዜን፥ የቃል ኪዳኔንም በዓላት፥ ሰንበታትንም፥ በመካከላቸውም የለየሁትን ቅድሳቴን፤ ስሜ በእርሱ ይጠራ ዘንድ፥ ያድርበትም ዘንድ በምድር መካከል ያከበርሁትን ድንኳኔንና መቅደሴን ትተዋልና። 10በዓላትን፥ መስገጃ ዛፍንና ጣዖትን ሠርተው ለመሳት እየራሳቸው ይሰግዳሉ። ልጆቻቸውንም ለአጋንንት፥ በልቡናቸው ስተው ለሠሩትም ጣዖት ሁሉ ይሠዋሉ፤ አዳኝባቸውም ዘንድ ወደ እነርሱ ምስክሮችን እልካለሁ። ነገር ግን አይሰሙም፤ ምስክሮችንም ይገድላሉ። 11ሕግን የሚሹ ሰዎችንም ይገድሉአቸዋል፤ ከሀገርም አስወጥተው ይሰድዱአቸዋል፤ ሁሉንም ያቦዝናሉ፤ በዐይኖችም ፊት ክፉ ሥራ መሥራትን ይጀምራሉ። 12ከእነርሱም ፊቴን እመልሳለሁ፤ ለመበዝበዝና ለመማረክ፥ ለመዘረፍም ይሆኑ ዘንድ በአሕዛብ እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከኢየሩሳሌምም መካከል አርቃቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል እበትናቸዋለሁ።
13“ሕጌን ሁሉ፥ ትእዛዜንም ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ፥ ሥርዐቴንም ሁሉ ይዘነጋሉ። የወሩን መባቻና ሰንበትን፥ በዓሉንና ኢዮቤልዩን፥ ሥርዐቱንም፥ ይዘነጋሉ። 14ከዚህም በኋላ በፍጹም ልባቸው፥ በፍጹም ነፍሳቸው፥ በፍጹም ኀይላቸውም ከአሕዛብ መካከል ወደ እኔ ይመለሳሉ። እኔም ከአሕዛብ ሁሉ መካከል እሰበስባቸዋለሁ። 15እገለጥላቸው ዘንድ ይፈልጉኛል። በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸውም በፈለጉኝ ጊዜ፥ እኔ በእውነት ብዙ ሰላምን እገልጥላቸዋለሁ፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ ወደ ቀና ሕግ እመልሳቸዋለሁ። 16ለበረከት ይሆናሉ፤ ለመርገምም አይደለም፤ ራስ ይሆናሉ፤ ጅራትንም አይደለም፤ በመካከላቸውም መቅደሴን እሠራለሁ፤ ከእነርሱም ጋር እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም በሚገባ በእውነት ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና አልተዋቸውም፤ አልለያቸውምም።”
17ሙሴም በግንባሩ ተደፍቶ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ አምላኬ፥ በልቡናቸው ስሕተት ይሄዱ ዘንድ ርስትህ የሆኑ ወገኖችህን አትተው። ይገዙአቸውም ዘንድ፥ አንተንም እንዲበድሉ ያደርጓቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው በአሕዛብ እጅ አትጣላቸው። 18አቤቱ፥ ይቅርታህ በወገኖችህ ላይ ከፍ ከፍ ይበል፤ የቀና ልቡናንም ፍጠርላቸው። በፊትህ ለማጣላት ፥ ከባለምዋልነትህም ይጠፉ ዘንድ ከእውነተኛ ሥራ ሁሉ ለማሰነካከል የዲያብሎስ መንፈስ አይሠልጥንባቸው። 19እነርሱስ በታላቅ ኀይልህ ከግብፅ ሰዎች እጅ ያዳንኻቸው ወገኖችህና ማደሪያዎችህ ናቸው። ንጹሕ ልቡናን ፍጠርላቸው። የተቀደሰ መንፈስንም አሳድርባቸው፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በኀጢአታቸው አይሰነካከሉ።”
20እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “እኔ ክርክራቸውንና አሳባቸውን አውቃለሁ፤ አንገታቸው ደንዳና ነው። ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኀጢአት እስኪያውቁ ድረስ አይሰሙም። 21ከዚህም በኋላ በፍጹም ቅንነት፥ በፍጹም ልቡናና በፍጹም ሰውነት ወደ እኔ ይመለሳሉ። የልቡናቸውን ቈላፍነትና የዘራቸውን ልቡና ቈላፍነት እቈርጣለሁ። ንጹሕ ልቡናንም እፈጥርላቸዋለሁ። 22ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ እንዳይመለሱ አነጻቸዋለሁ፤ ልቡናቸውም እኔን ትከተላለች፤ ትእዛዜንም ሁሉ ይፈጽማሉ። 23አባት እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ልጆች ይሆኑኛል፤ ሁሉም የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። መልአክ ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ያውቃቸዋል። እነርሱ ልጆች እንደ ሆኑ፥ እኔም በሚገባና በእውነት አባታቸው እንደ ሆንሁ፥ እንደምወድዳቸውም ያውቋቸዋል። 24አንተም በዚህ ተራራ ላይ እኔ የምነግርህን ይህን ነገር ሁሉ፥ የፊቱንና የኋላውን፥ ይመጣ ዘንድ ያለውንም፥ ሕጉና አምልኮቱም በሚነገሩበት በዓመቱ ቍጥር እስከ ዘለዓለም ድረስ የሚሆነውን የዘመኑን አከፋፈል ሁሉ፥ እኔም ወርጄ በዘመኑ ሁሉ ከእነርሱ ጋር እስክኖር ድረስ የሚደረገውን ሁሉ ጻፍ።”
25መልአከ ገጹንም እንዲህ አለው፥ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለዘለዓለም የምመሰገንበት ቤተ መቅደስ በመካከላቸው እስኪሠራ ድረስ እግዚአብሔርም ለሁሉ እስኪታይ ድረስ የሚሆነውን ለሙሴ ጻፍለት። 26እኔ የእስራኤል አምላክ እንደ ሆንሁ፥ ለያዕቆብ ልጆች ሁሉ አባት እንደ ሆንሁ፤ በደብረ ጽዮንም ለዘለዓለም ንጉሥ እንደ ሆንሁ ሁሉ ያውቃል፤ ጽዮን ኢየሩሳሌምም የከበረች ትሆናለች።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኩፋሌ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ