መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 36
36
የኢዮአክስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 23፥30-35)
1የሀገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት። 2ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሦስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። 2 ‘ሀ’ የእናቱም ስም ከሎቤና የኤርምያስ ልጅ አሚጣል ነበረች። 2 ‘ለ’ አባቶቹ እንደ ሠሩት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሠራ። በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ በኤማት ምድር በዴብላታ ፈርዖን ኒካዑ ማርኮ አሰረው።
3ንጉሡም ወደ ግብፅ ወሰደው፤ በሀገሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት። 4የግብፅም ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ የይሁዳን ንጉሥ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ ፋንታ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፤ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠ፤ ፈርዖን ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው። በዚያም ሞተ። 4 ‘ሀ’ ወርቅንና ብርን ለፈርዖን ሰጠ። በዚያን ጊዜም ምድር በፈርዖን ትእዛዝ ብር መገበሯን ጀመረች። 4 ‘ለ’ እያንዳንዱም እንደሚችለው ለፈርዖን ኒካዑ እንዲገብር ከሀገሪቱ ሕዝብ ወርቅንና ብርን ጠየቀ።
5ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘካራ የምትባል የኔሬያሳ ልጅ የራማ ሴት ነበረች፤ አባቶቹም እንዳደረጉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 5 ‘ሀ’ በእነዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚያ ሀገር መጣና ሦስት ዓመት ተገዛለት። ከእርሱም ከዳ።
5 ‘ለ’ እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን፥ የሞዓባውያንንና የአሞናውያንን ልጆችና የሰማርያን አደጋ ጣዮች ላከበት፤ ከዚህም በኋላ በአገልጋዮቹ በነቢያት እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ራቁ።
5 ‘ሐ’ ነገር ግን ምናሴ ስለሠራቸው ኀጢአቶችና ኢዮአቄም ስላፈሰሰው ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለ ሞላት ከፊቱ ይርቁ ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳ ላይ ነበር። 5 ‘መ’ እግዚአብሔርም ሊያጠፋቸው አልፈለገም ነበር።
6የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ ወጥቶ ወደ ባቢሎን ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። 7ናቡከደነፆርም ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አያሌውን አውጥቶ ወደ ባቢሎን ወሰደ፤ በባቢሎንም በጣዖቱ ቤት ውስጥ አኖረው። 8የቀሩትም የኢዮአቄም ነገሮች፥ ያደረገውም ርኵሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ ኢዮአቄምም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር በጋኖዛን ከተማ ተቀበረ።#“ኢዮአቄምም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ ከአባቶቹም ጋር በጋኖዛን ከተማ ተቀበረ” የሚለው በዕብ. የለም። ልጁም ኢኮንያን#ዕብ. “ዮአኪን” ይላል። ከእርሱ ቀጥሎ ነገሠ።
9ኢኮንያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስምንት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ነገሠ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 10ዓመቱም ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ የከበረውንም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ የአባቱን የኢዮአቄምን ወንድም#ዕብ. “ወንድሙን” ይላል። ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ።
11ሴዴቅያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። 12በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ከነቢዩ ከኤርምያስ ፊት፥ ከእግዚአብሔርም ቃል የተነሣ አላፈረም። 13ደግሞም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ። 14የይሁዳም ታላላቅ ሰዎች ካህናቱና የሀገሩም ሕዝብ በአሕዛብ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ። 15የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በነቢያቱ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። 16እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።
17ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጐልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ለንጉሣቸው ለሴዴቅያስም አልራራለትም፤ ደናግሉንም አልማረም፤ ሽማግሌዎቻቸውንም ወሰዳቸው፤ ሁሉንም እግዚአብሔር በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 18የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንም ቤት መዝገብ፥ የአለቆቹንም ቤት መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። 19የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሰ፤ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠለ፤ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፋ። 20የተረፉትንም ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የሜዶንም ንጉሥ እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤ 21በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፥ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች።
22በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ከተፈጸመ በኋላ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ በመንግሥቱም ሁሉ አዋጅ ይነገር ዘንድ በጽሕፈት እንዲህ ሲል አዘዘ፤ 23“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ እርሱም በይሁዳ ባለችው በኢየሩሳሌም ቤትን እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡም ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ይውጣ።”#ምዕ. 36 ቍ. 2“ሀ”፥ “ለ” እና “ሐ” ፤ ቍ. 4“ሀ” እና “ለ” ፤ ቍ. 5“ሀ”፥ “ለ”፥ “ሐ” እና “መ” በዕብ. የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 36: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ