መጽሐፈ ኩፋሌ 2
2
1በእስራኤል ሠራዊት ፊት የሚሄድ መልአከ ገጹም የዘመኖች አከፋፈል የተጻፈበትን ጽላት ያዘ። 2ይኸውም ለሕግና ለምስክርነት በሱባዔ የሚቈጠረው የዘመኑ አከፋፈል ከዓለም ፍጥረትና አዲስ ፍጥረት ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ፥ ሰማያትና ምድር፥ ፍጥረታቸውም ሁሉ የሰማይ ሠራዊት እንደ መሆናቸው እስኪታደሱ ድረስ ያለው የተጻፈበት ነው። 3የምድር ፍጥረት ሁሉ እንደ መሆናቸውም የእግዚአብሔር መቅደስ በኢየሩሳሌምና በደብረ ጽዮን እስኪሠራ ድረስ፥ ብርሃናትም ሁሉ ከእስራኤል ለተመረጡ ሰዎች ሁሉ ለደኅንነት፥ ለሰላምና ለበረከት ሊሆኑ እስኪታደሱ ድረስ፥ ከዚህች ቀን ጀምሮ እስከ ምድር ዘመን ሁሉ እንደዚሁ ይሆን ዘንድ የሚደረገው ሁሉ የተጻፈበት ነው።
4መልአከ ገጹም በእግዚአብሔር ቃል ሙሴን እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ እንደ ጨረሰ፥ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ 5በሰባተኛዪቱም ቀን እንዳረፈ፥ ከዕለታቱም ሁሉ እንደ ለያት፥ ለሥራውም ሁሉ ምልክት አድርጎ እንዳኖራት ጻፍ። በመጀመሪያዪቱ ቀን በላይ ያሉ ሰማዮችን ፈጥሮአልና፤ ምድርንና ውኃዎችንም፥ በፊቱ የሚያገለግል ፍጥረትንም ሁሉ ፈጥሮአልና። 6መላእክተ ገጽንም፥ የሚያመሰግኑ መላእክትንም፥ በእሳት አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ በነፋስ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በብርሃንና በጨለማ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ በበረድና በውርጭ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ 7በውኃ ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በነጐድጓድና በመብረቅ ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በቍርና በውርጭ፥ በክረምትና በመጸው፥ በጸደይና በበጋ፥ በሰማይና በምድር ባሉ ነፋሳት ሁሉ የተሾሙ መላእክትን፥ በወንዙ ሁሉ፥ በጨለማና በብርሃን፥ በንጋትና በምሽት በባሕርይ ዕውቀቱ ባዘጋጃቸው ላይ የተሾሙ መለእክትን ፈጥሮአልና።” 8ያንጊዜም ሥራውን አይተን ስለ ሠራው ሥራ ሁሉ በፊቱ ፈጽመን አመሰገንነው፤ በመጀመሪያዪቱ ቀን ሰባት ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶአልና።
9በሁለተኛዪቱም ቀን በሐኖስና በውቅያኖስ መካከል ጠፈርን አድርጎአልና፤ በዚያችም ቀን ውኃዎች ተከፍለው እኩሌቶቹ ወደ ላይ ወጥተዋልና፤ እኵሌቶቹ ከጠፈር በታች ወዳለው ወደ ምድር መካከል ወርደዋልና፤ በሁለተኛው ቀን ይህን ሥራ ብቻ ሠራ።
10በሦስተኛዪቱም ቀን፥ “ውኃዎች ከምድር ላይ ወደ አንዱ ቦታ ሄደው ይወሰኑ፥ ምድርም ትገለጥ” ብሎ እንደ ተናገረው አድርጎአልና። 11ውኃዎችም እንዳዘዛቸው እንደዚሁ ተዘጋጁ። ከምድር ፊት ወደ አንድ ቦታ ሄደው ከዚህ ከጠፈር በታች በውቅያኖስ ተወሰኑ፤ ምድርም ተገለጠች። 12በዚያችም ቀን በየመወሰኛቸው የባሕር ጥልቆችን ፈጠረላት፤ ፈሳሾችንም ሁሉ፥ የውኃዎችንም መወሰኛዎች፥ በተራራዎች ሥር በምድር ውስጥ ምንጮች ሁሉና በተራራዎች ሥር ያሉ የውኃዎችን መወሰኛዎች ሁሉ፥ በምድር ያሉ የውኃዎችንም ጕድጓድ ሁሉ ፈጠረላት። በየዘሩም የሚዘራውን ዘር፥ የሚበላውንም ዘር ሁሉ፥ የሚያፈሩ እንጨቶችንና ዛፎችንም፥ በገነትም ለተድላ የተፈጠሩ ተክሎችን፥ በሦስተኛዪቱ ቀን እነዚህን አራቱን ታላላቆች ፍጥረቶች ፈጠረ።
13በአራተኛዪቱም ቀን ጨረቃንና ፀሓይን፥ ከዋክብትንም ፈጥሮ በዓለሙ ሁሉ ያበሩ ዘንድ በጠፈር አኖራቸው። ሌሊትንና ቀንንም አስገዛቸው፤ በብርሃንና በጨለማ መካከልም ለመለየት ድንበር አደረጋቸው። 14እግዚአብሔርም በምድር ላይ ለቀኖችና ለሱባዔዎች፥ ለወሮችና ለበዓሎች፥ ለዓመታትና ለኢዮቤላት፥ በዓመት ለሚመላለሱ ሰዓቶችም ሁሉ ታላቅ ምልክት እንዲሆን፥ በብርሃንና በጨለማ መካከልም ድንበርን እንዲለይ፥ በምድርም ላይ የሚበቅለውና የሚያድገው ሁሉ ይድን ዘንድ፥ ለማዳን ፀሐይን ፈጠረ፤ በአራተኛዪቱ ቀን እነዚህን ሦስቱን ፍጥረቶች ፈጥረ።
15በአምስተኛዪቱም ቀን በጥልቅ ውኃዎች መካከል ያሉትን ታላላቅ ዓሣ አንበሪዎች ፈጠረ። ይህ ሁሉ መጀመሪያ በእጁ ተፈጥሮአልና፤ ሥጋዊ ደማዊ ሁሉ፥ በውኃዎችም ውስጥ የሚመላለስ ፍጥረት ሁሉ፥ ዓሣዎችና የሚበሩ ወፎች ሁሉ፥ ወገኖቻቸውም ሁሉ ተፈጥረዋልና፤ 16ፀሓይም ሕይወት ሊሆናቸው በእነርሱ ላይ ወጥቶአልና፥ በዚህ ዓለም በሚኖር ፍጥረትና በምድር በሚበቅለው ሁሉ ላይ፥ በሚያፈራውም እንጨት ሁሉ ላይ፥ በሥጋዊ ደማዊ ሁሉ ላይ ወጥቶአልና፤ በአምስተኛዪቱ ቀን እነዚህን ሦስቱን ፍጥረታት ሁሉ ፈጠረ።
17በስድስተኛዪቱም ቀን እንስሳትንና አራዊትን ሁሉ በምድር ላይ የሚመላለሰውንም ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኩፋሌ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ