ትንቢተ ኢዩኤል 2
2
አንበጣ የእግዚአብሔርን መምጣት እንደሚያመለክት
1በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ ዐዋጅ ንገሩ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይደንግጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፥ እርሱም ቀርቦአልና። 2የጨለማና የነፋስ ቀን፥ የደመናና የጉም ቀን ነው፤ ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፤ ከዘለዓለምም ጀምሮ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም፤ ከእርሱም በኋላ እስከ ልጅ ልጅ ድረስ እንደ እርሱ ያለ አይሆንም። 3እሳት በፊታቸው ትበላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፤ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ደስታ ገነት፥ በኋላቸውም እንደ ምድረ በዳ በረሃ ናት፤ ከእርሱም የሚያመልጥ የለም።
4መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤ እንደ ፈረሶችም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እንደ ፈረሰኞች” ይላል። ይሮጣሉ። 5ድምፃቸውም በተራራ ላይ እንደ አሉ ሠረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ ነው፤ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብዙና ብርቱ ሠራዊት ያኰበኵባሉ። 6ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፤ የሰውም ፊት ሁሉ እንደ ድስት ጥላሸት ይጠቍራል። 7እንደ ተዋጊዎች ይሮጣሉ፤ እንደ ጦረኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፤ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፤ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም። 8አንዱ ከሌላው ርቆ አይቆምም፤ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ይሮጣሉ፤ በመሣሪያቸው ላይ ይወድቃሉ፤ እነርሱም አይጠፉም። 9ከተሞችን ይይዛሉ፤ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፤ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፤ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ። 10ምድሪቱም ከፊታቸው ትደነግጣለች፤ ሰማይም ይንቀጠቀጣል፤ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ። 11እግዚአብሔርም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ይሰጣል፤ ሰፈሩ እጅግ ብዙ ነውና፥ የቃሉም ሥራ ጽኑዕ ነውና፤ የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የምታስፈራ ናትና፥ ፈጽማ ትገለጣለች፥ መጠኗ ምንድን ነው? ማንስ ይችላታል?
12አሁንስ ይላል አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ “በፍጹም ልባችሁ በጾም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። 13ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፥ ቍጣው የዘገየ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።” 14የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቍርባን የሚሆን በረከትን በኋላ የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
15በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ 16ሕዝቡንም ሰብስቡ፤ ማኅበሩንም ቀድሱ፤ ሽማግሌዎቹንም ጥሩ፤ ጡት የሚጠቡትንና ሕፃናትን ሰብስቡ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራዪቱም ከጫጕላዋ ይውጡ። 17የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናት በወለሉና በምሥዋዑ መካከል እያለቀሱ፥ “አቤቱ! ለሕዝብህ ራራ፤ አሕዛብም ይገዙአቸው ዘንድ ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤ ከአሕዛብም መካከል፦ አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ?” ይበሉ።
18እግዚአብሔርም ስለ ምድሩ ቀና፤ ለሕዝቡም ራራለት። 19እግዚአብሔርም መልሶ ሕዝቡን፥ “እነሆ እህልንና ወይንን፥ ዘይትንም እሰድድላችኋለሁ፤ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም። 20የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ፤ ወደ በረሃና ወደ ምድረ በዳ እሰደዋለሁ፤ ፊቱን ወደ መጀመሪያው#ዕብ. “ምሥራቁ” ይላል። ባሕር፥ ጀርባውንም ወደ ኋለኛው#ዕብ. “ምዕራብ” ይላል። ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፤ እርሱም ትዕቢትን አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፤ ክርፋቱም ይነሣል።”
21“ምድር ሆይ! አትፍሪ፤ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአልና ፈጽሞ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ። 22እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ! የምድረ በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኀይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ። 23እናንተ የጽዮን ልጆች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ምግብን በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ ቀድሞውም የበልጉንና የመከሩን ዝናብ ያዘንብላችኋልና። 24ዐውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፤ መጭመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ። 25የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ፥ ኩብኩባና ተምች ስለ በላቸው ዓመታት እመልስላችኋለሁ። 26ብዙ መብል ትበላላችሁ፤ ትጠግቡማላችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም። 27እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም።
28“ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢትን ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ፤ 29ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ። 30በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። 31ታላቋና ግልጥ የሆነችው#ዕብ. “የሚያስፈራው” ይላል። የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። 32እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ይድናሉ። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፥ የምሥራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ።#ምዕ. 2 ከቍ. 28 እስከ 32 ያለው በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 3 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢዩኤል 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ