መጽሐፈ ኢዮብ 38
38
እግዚአብሔር ለኢዮብ እንደ መለሰለት
1ኤልዩስ ንግግሩን ካቆመ በኋላ እግዚአብሔር በደመናና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን ጠየቀው፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ተናገረው” ይላል። እንዲህም አለው፦
2“ከእኔ ምክርን የሚሸሽግ፥
በልቡም ነገርን የሚደብቅ ማን ነው?
ከእኔ ይሰውረዋልን?
3እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤
እጠይቅሃለሁ፥ አንተም መልስልኝ።
4ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?
ታስተውል እንደ ሆነ ንገረኝ።
5ብታውቅ መስፈሪያዋን የወሰነ፥
በላይዋስ የመለኪያ ገመድን የዘረጋ ማን ነው?
6መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር?
የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?
7ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ
መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምፅ አመሰገኑኝ#ዕብ. “የእግዚአብሔር ልጆች” ይላል።
8ከእናቷ ማኅፀን በወጣች ጊዜ፥
ባሕርን በመዝጊያዎች ዘጋኋት፤
9ደመናውን ልብስ አደረግሁላት።
በጭጋግም ጠቀለልኋት።
10ድንበርም አደረግሁላት።
መወርወሪያዎችንና መዝጊያዎችንም አኖርሁ።
11እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ ከወሰንሽም አትለፊ፤
ነገር ግን ማዕበልሽ በመካከልሽ ይገደብ አልኋት።
12“የንጋት ወገግታ በአንተ ተፈጥሮአልን?
የአጥቢያ ኮከብስ ትእዛዙን በአንተ ዐውቋልን?
13የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥
ከእርስዋም ኃጥኣንን ያናውጥ ዘንድ።
14አንተ ጭቃውን ከመሬት ወስደህ
ሕያው ፍጥረትን ፈጥረሃልን?
በምድርስ ላይ እንዲናገር አድርገሃልን?
15የኃጥኣንን ብርሃናቸውን ከልክለሃልን?
የትዕቢተኞችንስ ክንድ ሰብረሃልን?
16ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን?
በጥልቁስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን
17ከግርማህስ የተነሣ የሞት በሮች ተከፍተውልሃልን?
የሲኦል በረኞችስ አንተን አይተው ይደነግጣሉን?
18ከሰማይ በታች ያለ የምድርንስ ስፋት አስተውለሃልን?
መጠኑም ምን ያህል እንደ ሆነ እስኪ ንገረኝ!
19“የብርሃን ማደርያው ቦታ የት ነው?
የጨለማስ ቦታው ወዴት አለ?
20ትችል እንደ ሆነ፥
መንገዳቸውንም ታውቅ እንደሆነ፥
ወደ ዳርቻቸው እስኪ ውሰደኝ።
21በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥
የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥
በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።
22በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን?
የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን?
23ይህስ በጠላትህ ጊዜ
ለሰልፍና ለጦርነት ቀን ይጠበቅልሃልን?
24አመዳይ ከየት ይወጣል?
ከሰማይ በታች ያለ የአዜብ ነፋስስ እንዴት ይበተናል?
25ለኀይለኛው ዝናብ መውረጃውን፥
ወይስ ለሚያንጐዳጕደው መብረቅ መንገድን ያዘጋጀ ማንነው?
26ማንም በሌለበት ምድር ላይ፥
ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ ይዘንም ዘንድ፥
27ባድማውንና ውድማውን ያጠግብ ዘንድ፥
ሣሩንም በምድረ በዳ ያበቅል ዘንድ፥
28የዝናብ አባቱ ማን ነው?
ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?
29በረዶስ ከማን ማኅፀን ይወጣል?
የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?
30እርሱም እንደ ፈሳሽ ውኃ ይወርዳል።
ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥
የኃጥኣንንስ ፊት ማን አዋረደ?#ዕብ. “የቀላዩም ፊት ረግትዋል” ይላል።
31“በውኑ የሰባቱን ከዋክብት#በግእዝ “ትርያ” በግሪክ ሰባ. ሊ. “ፕሊአዛ” ይላል። ዘለላ ታስር ዘንድ፥
ወይስ ኦሪዮን#ግእዙ “ደብራን” ይላል። የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?
32ወይስ ማዛሮት#በግእዝ “ብልአተናሽ” ይላል። የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥
ወይስ የምሽቱን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?
33የሰማይን ሥርዐት፥
ከሰማይ በታችስ የሚሆነውን ታውቃለህን?
34ደመናውን በቃልህ ትጠራዋለህን?
ብዙ ውኃስ እየተንቀጠቀጠ ይመልስልሃልን?
35መብረቁን ትልከዋለህን? እርሱስ ይሄዳልን?
ደስታህስ ምንድን ነው ይልሃልን?
36ለሴቶች የፈትልን ጥበብና
የተለያዩ የጥልፍ ሥራዎችን ዕውቀት ማን ሰጠ?
37የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው?
ሰማይንም ወደ ምድር ያዘነበለ ማን ነው?
38እንደ ትቢያ በምድር ተዘርግቷል፤
እንደ ዓለት ድንጋይም አጣበቅሁት።
39“ለአንበሳዪቱ አደን ታድናለህን?
የእባቦችንስ ነፍስ ታጠግባለህን?
40በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው
በጫካም ውስጥ አድብተው ይቀመጣሉና።
41ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥
የሚበሉትም ፈልገው ሲቅበዘበዙ፥
ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 38: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ