መጽሐፈ ኢዮብ 37
37
1“ስለዚህም ልቤ ደነገጠችብኝ፥
ከስፍራዋም ተንቀሳቀሰች።
2የእግዚአብሔርን የቍጣውን ድምፅ ስማ፥
ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጥ።
3እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥
ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል።
4በስተኋላው ድምፅ ይጮኻል፤
በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤
ድምፁም በተሰማ ጊዜ ሰዎች እንዲጠፉ አያደርግም።
5ኀያሉ እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅ አድርጎ ያንጐደጕዳል፤
ለእንስሳት በየጊዜው ምግባቸውን ያዘጋጃል፥ የሚተኙበትንም ጊዜ ያውቃሉ፤
በዚህ ሁሉ ልብህ አይደንግጥብህ፤
ሥጋህም ልብህም ከግዘፉ አይለወጥብህ፤
እርሱም እኛ የማናውቀውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።#ምዕ. 37 ቍ. 5 ላይ 2ኛ፥ 3ኛ እና 4ኛ መስመሮች በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 36 ቍ. 28 ይገኛል።
6በረዶውንና ውሽንፍሩን፥ ብርቱውንም ዝናብ
በምድር ላይ እንዲወርድ ያዝዛል።
7ሰው ሁሉ ደካማነቱን ያውቅ ዘንድ፥
የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል።
8አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥
በዋሾቻቸውም ያርፋሉ።
9ከተሰወረ ማደሪያውም ችግር፥
ከተራሮች ጫፍም ብርድ ይመጣል።
10ከኀያሉ እግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ይመጣል።
ውኃውንም እንደ ወደደ ይመራዋል።
11የተመረጡትን በደመና ይሰውራል፤#በዕብራይስጥ ይለያል።
ብርሃኑም ደመናውን ይበትናል፤
12እርሱም ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ፥
ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ፥
ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል።
13ይኸውም፥ ለተግሣጽ
ወይም ለምድሩ ወይም በምሕረት ለሚያገኘው እንዲሆን ነው።
14“ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤
ቁም፥ በእግዚአብሔርም ኀይል ተገሠጽ።
15እግዚአብሔር ሥራውን እንዳከናወነ
ከጨለማም ለይቶ ብርሃንን እንደ ፈጠረ እናውቃለን።#በዕብራይስጥ ይለያል።
16የደመናትን ክፍሎች፥
አስፈሪ የሆነውንም የኀጢአተኞችን አወዳደቅ ያውቃል።
17የአዜብ ነፋስ በተኮሰ ጊዜ ያንተ ልብስህ የሞቀ ነው።
እንግዲህ በምድር ላይ ፀጥ በል።
18እንደ ቀለጠ መስተዋት
ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን?
19ስለዚህ ንገረኝ! ምን እንለዋለን?
እንግዲህ ዝም እንበል፥ ብዙም አንናገር፥
20“ሰው በእኔ ዘንድ ሲቆም ዝም እል ዘንድ፥
መጽሐፍ ወይም ጸሓፊ አለኝን?#በዕብራይስጥ ይለያል።
21“ብርሃን ለሁሉ የሚታይ አይደለም
ብርሃን በእርሱ ዘንድ በደመና ውስጥ ሆኖ
ከሩቅ በሰማያት ያበራል።
22ከሰሜን እንደ ወርቅ የሚያበራ ደመና ይወጣል፤
በዚህም ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔር ታላቅ ክብርና ምስጋና አለ።
23በኀይል ከእርሱ ጋር እኩል የሚሆን፥#በዕብራይስጥ ይለያል።
እውነትንም የሚፈርድ ሌላ አናገኝም።
እርሱ እንደማይሰማ ታስባለህን?
24ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤
በልባቸውም ጠቢባን የሆኑ ሁሉ ይፈሩታል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 37: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ