መጽሐፈ ኢዮብ 36
36
የኤልዩስ መጨረሻ ንግግር
1ኤልዩስም ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“ገና የምናገረው ነገር አለኝና ጥቂት ታገሠኝ፥
እኔም አስተምርሃለሁ።
3ዕውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥
ሥራዬንም እውነት ነው እላለሁ።
4ቃሌ ሐሰት ያይደለ እውነት ነው።
አንተም የዐመፅ ቃላትን አትሰማም።
5“በጥበብ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ጥበብ” ይላል። ብርቱና ኀያል የሆነ እግዚአብሔር፥
የዋሁን ሰው እንደማይጥለው ዕወቅ።
6እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤
ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል።
7ዐይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፤
ለዘለዓለም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥
በድል አድራጊነትም ያኖራቸዋል።
እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።
8በሰንሰለት እጃቸውን የታሠሩ
በችግር ገመድ ይያዛሉ።
9ሥራቸውንና መተላለፋቸውን ይነግራቸዋል፥
ብዙ ነውና።
10ጻድቃንን ግን ይሰማቸዋል፥
ከኀጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።
11ቢሰሙና ቢያገለግሉትም፥
ዕድሜአቸውን በመልካም፥
ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።
12ኃጥኣንን ግን አያድናቸውም
እግዚአብሔርን ያዩ ዘንድ አይወዱምና፥
ሲገሥፃቸውም አይሰሙምና።
13“ግብዞች ግን በልባቸው ቍጣን ያዘጋጃሉ፤
እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም።
14ስለዚህም በሕፃንነታቸው ሳሉ ሰውነታቸው ትጠፋለች፥
ሕይወታቸውንም መላእክት ያጠፉአታል።
15የተቸገረውንና ረዳት የሌለውን አስጨንቀዋልና፥
የየዋሃንንም ፍርድ ለውጠዋልና።
16አንተን ግን ከጠላትህ አፍ አድኖሃል፥#በዕብራይስጥ ይለያል።
በበታችህም ጥልቅ ባሕር፥ ፈሳሽ ምንጭም አለ፥
ማዕድህም በስብ ተሞልታ ትወርዳለች።
17ፍርድን ለጻድቃን አያዘገይምና።
18ይበድሉ ዘንድ በተቀበሉት መማለጃ ኀጢአት ምክንያት
ቍጣ በኃጥኣን ላይ ትመጣለች።#በዕብራይስጥ ይለያል።
19በጭንቀት ካሉ ከችግረኞች ልመና የተነሣ
አእምሮህ በፈቃድ አያስትህ#በዕብራይስጥ ይለያል።
20በእነርሱ ፋንታ ወገኖች እንዲገቡ፥
ኀያላን ሰዎችን ሁሉ በሌሊት አታስወጣ።
21መልካምን አድርግ እንጂ፥
ክፉን እንዳትሠራ ተጠንቀቅ።
ስለዚህም ከችግር ትድናለህ።
22“እነሆ፥ ኀያሉ እግዚአብሔር በኀይሉ ያጸናል።
እንደ እርሱስ ያለ ኀያል ማን ነው?
23ሥራውንስ የሚመረምር ማን ነው?
ወይስ፦ ክፉ ሠርተሃል የሚለው ማን ነው?
24ሰዎች ሊሠሩት ከሞከሩት በላይ፥
ሥራው ታላቅ እንደ ሆነ አስብ።
25ሰው ሁሉ ራሱ፥
ኃጥኣን ሙታን እንደ ሆኑ ያስባል።
26እነሆ፥ ኀያሉ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም፤
የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።
27የዝናቡም ነጠብጣቦች በእርሱ ይቈጠራሉ።
ዝናብም ከደመና ይንጠባጠባል፤
28የጥንቱ ይበቅላል።
ደመናም በሟች ላይ ይጋርዳል፥
ስፍር ቍጥር የሌለው ዝናብ ይዘንባል፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. የሚከተለውን ይጨምራል “ ለእንስሳትም ጊዜን ይወስናል ፤ እነርሱም የዕረፍትን ሥርዐት ያውቃሉ ፤ ይህንም ሁሉ በማወቅህ አትደነቅ ፤ አእምሮህም በሰውነትህ አይታወክ፤”
29አንድ ሰው የደመናውን መዘርጋት፥
ወይም የማደሪያውን ልክ ቢያውቅ፥
30እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ቀስቱን በእርሱ ላይ ይዘረጋል” ይላል።
የባሕሩንም ጥልቀት ይከድነዋል።
31በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤
ለኀይለኛውም ምግቡን ይሰጠዋል።
32በእጁ ብርሃንን ይሰውራል፥#የግእዙ ምዕ. 36 ቍ. 32 እና 33 ግልጥ አይደለም።
አደጋ የሚጥልባትንም አዘዘ።
33ስለ እርሱም ወዳጁ፥
በዐመፃው ያገኘችውን ይናገራል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 36: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ