መጽሐፈ ኢዮብ 29
29
የኢዮብ መጨረሻ ንግግር
1ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ፦
2“እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥
ወደ ፊተኛው ወራት ማን በመለሰኝ?
3በራስጌዬ ላይ መብራቴ በበራ ጊዜ፥
እኔም ጨለማውን ዐልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥
4በበረከት ሁሉ በነበርሁ ጊዜ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መንገዴን እከተል በነበርሁ ጊዜ” ይላል።
እግዚአብሔርም ቤቴን በጐበኘ ጊዜ፥
5ባለ ሀብት በነበርሁ ጊዜ፥
ልጆችም በዙሪያዬ በነበሩ ጊዜ፥
6ቅቤ በመንገዴ ይፈስስ በነበረ ጊዜ፥
ወተት በተራራዬ ይፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7ወደ ከተማዪቱ ገሥግሼ በወጣሁ ጊዜ፥
በአደባባዩም ወንበሬን ባኖሩልኝ ጊዜ፥
8ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥
ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9ኀያላኑም ከመናገር ዝም አሉ፥
እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
10የሰሙኝም ብፁዕ ይሉኛል።
ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጠጋ።
11የሰማችኝም ጆሮ ብፁዕ አለችኝ፥
ያየችኝም ዐይን ገለል አለች፤
12ድሃውን ከሚጨቁነው እጅ አድኛለሁና።
ረዳት የሌለውን ደሃአደጉንም ረድቸዋለሁና።
13ለሞት የቀረበው መረቀኝ፤
የባልቴቲቱም አፍ ባረከኝ፤
14ጽድቅን ለበስሁ፥
ቅንነትንም እንደ መጎናጸፊያ ተሸለምሁ፤
ፍርድንም እንደ ኩፋር ተቀዳጀኋት
15ለዕውራን ዐይን፥
ለአንካሳዎችም እግር ነበርሁ።
16ለድሃዎች አባት ነበርሁ፥
የማላውቀውንም ሰው ክርክር መረመርሁ።
17የኀጢአተኞችን መንጋጋ ሰበርሁ፥
የነጠቁትንም ከጥርሳቸው ውስጥ አስጣልሁ።
18እኔም እንደምሸመግልና እንደማረጅ፥
እንደ ረዥም ዘንባባም ረዥም ዘመን እንደምኖር፥
እንደ አሸዋም ዘመኔን እንደማበዛ ዐሰብሁ።
19ውኃ በሥሬ ላይ ይፈስሳል፥
ጠልም በአዝመራዬ ላይ ይወርዳል፤
20ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥
ቀስቴም በእጄ ውስጥ ሳለ እሄዳለሁ።
21“ሰዎች እኔን ይሰሙኛል፥ ያዳምጡኝማል፥
በምክሬም ዝም ይላሉ።
22በነገሬ ላይ ደግመው አይናገሩም፤
ባነጋገርኋቸውም ጊዜ ደስ ይላቸዋል።
23የተጠማች ምድር ዝናምን ተስፋ እንደምታደርግ፥
እንደዚሁም እነርሱ ንግግሬን ይጠባበቃሉ።
24በእነርሱ ብስቅ አያምኑም፤
የፊቴም ብርሃን አልወደቀም።
25መንገዳቸውን መረመርሁ፤
እንደ አለቃም ሆኜ ተቀመጥሁ፤
ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር ኖርሁ፤
በሚያዝኑም ጊዜ በእኔ ይጽናኑ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 29: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ