መጽሐፈ ኢዮብ 28
28
1“በእውነቱ ብር የሚወጣበት ቦታ አለ፥
ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2ብረትም ከመሬት ውስጥ ይወጣል፤
መዳብም እንደ ድንጋይ ይፈለጣል።
3ለጨለማ ወሰንን ያደርጋል፤
እርሱ ሁሉን ይመረምራል፥
የጨለማንና የሞት ጥላ ድንጋይንም ይመረምራል።
4በአፈር ምክንያት እንደሚከፈል ወንዝ
የጽድቅን መንገድ የረሱ በኀጢአታቸው ይደክማሉ።
ከሰዎችም መካከል ይለያሉ። #በዕብራይስጥ ልዩነት አለው።
5እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤
በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል።
6ድንጋይዋ እንደ ሰንፔር፥
ወርቅዋም እንደ አፈር የሆነ መሬት አለች።
7መንገድዋን ዎፍ አያውቀውም፥
የንስርም ዐይን አላየውም።
8የትዕቢተኞች ልጆች አልረገጡአትም፥
ደቦል አንበሳም በውስጥዋ አላለፈባትም።
9ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥
ተራራዎችንም ከመሠረታቸው ይገለብጣቸዋል።
10ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤
ዐይኔም የከበረውን ነገር ሁሉ ታያለች።
11የፈሳሹንም ጥልቀት ይገልጣል።
ኀይሉንም በብርሃን ይገልጣል።
12“ነገር ግን ጥበብ ወዴት ትገኛለች?
የጥበብስ ሀገርዋ ወዴት ነው?
13ሟች ሰው መንገድዋን አያውቅም፤
በሰዎችም ዘንድ አትገኝም።
14ቀላይ፦ በእኔ ውስጥ የለችም ትላለች።
ባሕርም፦ በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።
15ስለ እርስዋም ማንም ምዝምዝ ወርቅ አይሰጥም
ብርም በእርስዋ ለውጥ አይመዘንም።
16ከአፌር ወርቅም ጋር አትወዳደርም።
በከበረ መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥
የወርቅም ጥሬ ዕቃ የእርስዋ ለውጥ አይሆንም።
18ዛጎልና አልማዝ አይታሰቡም።
አንተ ግን እጅግ ከከበሩ ነገሮች ሁሉ ይልቅ
ጥበብን አቅርባት።
19የኢትዮጵያ ሉል አይተካከላትም፥
በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
20“እንግዲያ ጥበብ ከወዴት ትገኛለች?
የማስተዋልስ ሀገሯ ወዴት ነው?
21በሰው ሁሉ ዘንድ ተረስታለች፥
ከሰማይ ወፎችም ተሰውራለች።
22ሞትና ሲኦል ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።
23“እግዚአብሔር መንገድዋን አሳመረ፥
እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።
24እርሱም በሰማይ ያለውን ይመለከታል፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ ...” ይላል።
በምድርም ያለውን ሁሉ ያውቃል።
25ለነፋስ ሚዛንን
ለውሆችም መስፈሪያን አደረገ።
26እነዚህን በፈጠረ ጊዜ እንዲሁ ዐውቆ ቈጠራቸው።
ለዝናም ሥርዐትን ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን አደረገ።
27በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤
አዘጋጃትም፥ አከበራት፥ ደግሞም መረመራት።
28ሰውንም፦ ‘እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤
ከክፉ መራቅም ማስተዋል ነው’ ” አለው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 28: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ