መጽሐፈ ኢዮብ 27
27
1ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ እንዲህም አለ፦
2“እንደዚህ የፈረደብኝ ሕያው እግዚአብሔርን!
ነፍሴንም መራራ ያደረገ ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን!
3እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ ገና ሳለች፥
የሚያናግረኝም የእግዚአብሔር መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥
4አንደበቴ ዐመፅን አይናገርም፤
ነፍሴም የዐመፅ አሳብን አትማርም፤
5እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፤
እስክሞትም ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅምና።
6ጽድቅን እየሠራሁ አልጠፋም፤
ያደረግሁት ክፉ ነገር አይታወቀኝምና።
7ጠላቶች እንደ ኀጢአተኞች ውድቀት፥
በእኔ ላይም የሚነሡ እንደ በደለኞች ጥፋት ይሁኑ።
8“ኀጢአተኛ ድኅነትን ተስፋ ያደርግ ዘንድ ለምን ደጅ ይጠናል?
በእግዚአብሔርስ የማያምን ይድናልን? እንጃ!#በዕብራይስጥ ታላቅ ልዩነት አለው።
9በውኑ መከራ በመጣበትስ ጊዜ፥
ጸሎቱን ይሰማዋልን?
10በእርሱ ዘንድስ ባለሟልነትን ያገኛልን?
እግዚአብሔርንስ በጠራ ጊዜ ይመልስለታልን?
11እኔ ግን በእግዚአብሔር እጅ ምን እንዳለ አስተምራችኋለሁ፤
ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውንም አልዋሽም።
12እነሆ፥ ሁላችሁም፥
በክፉዎች ላይ ክፋት እንደምትመጣባቸው ታውቃላችሁ።
13ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ የኀጢአተኛ እድል ፋንታ ናት፥
ግፈኞችም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበሏት ሀብት ናት።
14ልጆቹ ቢበዙ ለጥፋት ይሆናሉ፤
ቢያድጉም ለማኞች ይሆናሉ።
15ለእርሱም የቀሩት ፈጽመው ይሞታሉ።
ለመበለቶቻቸውም የሚያዝንላቸው የለም።
16እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢሰበስብ፥
ወርቅንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥
17ይህን ሁሉ ጻድቃን ይወስዱታል።
ሀብቱንም ቅኖች ይከፋፈሉታል።
18ቤቱ እንደ ሸረሪት ድር፥
ቅንቅንም እንደሚበላው ይሆናል።
19ባለጠጋ ይተኛል፥ የሚያነቃውም የለም፤#በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩነት አለው።
ዐይኖቹን ይከፍታል፥ ይደነቃልም።
20ሥቃይ እንደ ጎርፍ ታገኘዋለች፤
በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች።
21የሚያቃጥል ነፋስ ያነሣዋል፥
እርሱም ያልፋል፤ ከቦታውም ይጠርገዋል።
22በእርሱም ላይ የማያውቀው ይመጣበታል፤
አይራራለትም፥ ከእጁም ፈጥኖ መሸሽ ይወድዳል።
23በእርሱም እጁን ያጨበጭብበታል፤
ከስፍራውም በፉጨት ጎትቶ ያወጣዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 27: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ