መጽሐፈ ኢዮብ 20
20
የሶፋር ሁለተኛ ንግግር
1አሜናዊውም#ዕብ. “ናዕማታዊው” ይላል። ሶፋር መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“እንደዚህ እንደምትመልስ አልጠረጠርሁህም ነበር፤
በዕውቀትም ከእኔ አትሻልም።
3የትምህርቴን ጥበብ ልንገርህ፤ ስማኝ፤
የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል።
4ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ፥ ከድሮ ዘመን ጀምሮ፥
በአንተስ ዘመን እንደዚህ ያለ ነገር ታውቃለህን?
5የኀጢኣተኞች ደስታ ታላቅ ሰልፍ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የውድቀት ምልክት” ይላል። ነው፥
የዝንጉዎችም ደስታ ጥፋት ነው።
6መባው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥
መሥዋዕቱም እስከ ደመና ቢደርስ፥
7እነሆ ተደላድያለሁ በሚልበት ጊዜ ለዘለዓለም ይጠፋል።
የሚያውቁትም ወዴት ነው? ይላሉ።
8እንደ ሕልም ይበርራል፤ እርሱም አይገኝም፤
ሲነጋም እንደማይታወቅ እንደ ሌሊት ራእይ ይሰደዳል።
9ዐይን አየችው፤ ነገር ግን ዳግመኛ አታየውም፤
ስፍራውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያውቀውም።
10የተዋረዱ ሰዎች ልጆቹን ያጠፋሉ፤
እጆቹም የኀዘን እሳትን ያቀጣጥላሉ።
11ጭንቀት በአጥንቶቹ ሞልቶአል፤
ነገር ግን ሕማሙ ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።
12“ክፋት በአፉ ውስጥ ብትጣፍጠው፤
ከምላሱም በታች ቢሰውራት፥
13ቢጠብቃትም፥ ባይተዋትም፤
በጕሮሮውም መካከል ቢይዛት፥
መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፤
14ፈጽሞ ራሱን መርዳት አይችልም።
የእፉኝትም መርዝ ከከንፈሩ በታች አለ።
15በዐመፅ የሚሰበሰብ ሀብትም ይጠፋል፤
የሞት መልአክም ከቤቱ ውስጥ እያዳፋ ያወጣዋል።
16የእባብን መርዝ ይጠባል፤
የእፉኝትም ምላስ ይገድለዋል።
17የመንጋዎቹንም ጥጆች፥
የማሩንና የቅቤውንም ፈሳሽ አይመለከትም።
18ለማይቀምሰው፥ ለማይታኘክና ለማይዋጥ ሀብት
በከንቱ ይደክማል።
19የደካሞችን ቤቶች አፍርሶአልና፤
ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአልና።
20ለንብረቱ ጥበቃ የለውም፤
የወደደውንም ነገር አያገኝም።
21ለሀብቱ ትርፍ የለውም፤
ስለዚህ በረከቱ አትከናወንለትም።
22በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፤
መከራም ሁሉ ያገኘዋል።
23“ሆዱን ቢያጠግብ፥
የመዓት መቅሠፍት ይጨመርበታል፤
የሕማሙም ሥቃይ ይጸናበታል።
24ከሰይፍም ኀይል አያመልጥም፤
የናስም ቀስት ይወጋዋል።
25ቀስቱም በሥጋው ውስጥ ያልፋል።
ክፉም ነገር በሰውነቱ ይመላለሳል፤
ፍርሀትም ይወድቅበታል።
26ጨለማ ሁሉ ይጠብቀዋል፤
ዕፍ የማይባል እሳትም ይበላዋል፤
እንግዳም ቤቱን ያጠቃዋል።
27ሰማይ ኀጢኣቱን ይገልጥበታል፤
ምድርም በእርሱ ላይ ትነሣለች።
28ጥፋትም ቤቱን ወደ ፍጻሜ ያመጣታል።
የቍጣ ቀንም ትመጣበታለች።
29ከእግዚአብሔር ዘንድ የኀጢአተኛ ሰው እድል ፋንታው፥
ከሚያየው ከፈጣሪውም የተመደበ ርስቱ ይህ ነው።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ