ትንቢተ ኤርምያስ 44
44
በግብፅ ለሚኖሩ አይሁድ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል
1በግብፅ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ፥ በሜምፎስም፥ በፋቱራም ሀገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፦ 2“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ አይታችኋል፤ ከክፋታቸውም የተነሣ እነሆ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፤ የሚቀመጥባቸውም የለም። 3ይህም የሆነው ያስቈጡኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት፥ እነርሱና አባቶቻቸው ለማያውቁአቸው ለሌሎች አማልክት ያጥኑ ዘንድ፥ ያመልኳቸውም ዘንድ ስለሄዱ ነው። 4በማለዳም ባሪያዎችን ነቢያትን ሁሉ ላክሁባቸው፤ የጠላሁትንም ርኩስ ነገር አታድርጉ ብዬ ላክሁባቸው። 5ነገር ግን አልሰሙኝም፤ ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት እንዳያጥኑ ጆሮአቸውን አልመለሱም። 6ስለዚህ መዓቴና መቅሠፍቴ ወረደ፤ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደደ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ጠፍና ባድማ ሆኑ።
7“አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ቅሬታ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ብላቴናንና የሚጠባ ሕፃንን ከመካከላችሁ ታጠፉ ዘንድ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? 8ሰውነታችሁንም ታጠፉ ዘንድ፥ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ ትሆኑ ዘንድ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብፅ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ? 9በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የአለቆቻቸውንም ክፋት#“የአለቆቻቸውንም ክፋት” የሚለው በዕብ. የለም። “የሚስቶቻቸውን ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት” የሚል ዕብ. ይጨምራል። የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን?። 10እስከ ዛሬም ድረስ አላረፉም፤ አልፈሩምም፤ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዐቴ አልሄዱም።
11“ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይሁዳን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በግብፅ ያሉ የአይሁድን ቅሬታ” ይላል። ሁሉ አጠፋ ዘንድ፥ ፊቴን ለክፋት በላያችሁ አደርጋለሁ። 12ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ፥ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ቅሬታ እወስዳለሁ፤ ሁሉም ይጠፋሉ፤ በግብፅም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለጥፋት፥ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ። 13ኢየሩሳሌምንም በመዐት እንደ ጐበኘሁ፥ እንዲሁ በግብፅ ምድር የሚኖሩትን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እጐበኛለሁ። 14በዚያ ለመቀመጥ በልባቸው ተስፋ ወደሚያደርጓት ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሱ ዘንድ በግብፅ ለመኖር ከመጡ ከይሁዳ ቅሬታ ወገን የሚያመልጥና የሚቀር፥ ወደዚያም የሚመለስ አይኖርም፤ ከሚያመልጥም በቀር ማንም አይመለስም።”
15ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ፥ በዚያም የቆሙ ሴቶች ሁሉ፥ በግብፅም ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት፤ እንዲህም አሉ፦ 16“አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማም። 17ነገር ግን እኛና አባቶቻችን፥ ነገሥታቶቻችንም፥ አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ እናደርገው እንደ ነበረ፥ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ፥ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያ ጊዜም እንጀራን እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ነበር፤ ክፉም አናይም ነበር። 18ለሰማይ ንግሥት ማጠንን፥ ለእርስዋም የመጠጥን ቍርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ ሁላችን አንሰናል፤ በሰይፍና በራብም አልቀናል። 19እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት፥ የመጠጥንም ቍርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ምስልዋን ለማበጀት እንጎቻ አድርገንላት ኖሮአልን? የመጠጥንም ቍርባን አፍስሰንላት ኖሮአልን?”
20ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፦ ለወንዶቹና ለሴቶቹ፥ ለሕዝቡም ሁሉ መለሰላቸው እንዲህም አለ፦ 21“እናንተና አባቶቻችሁ፥ ነገሥታቶቻችሁም፥ አለቆቻችሁም የምድርም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን እግዚአብሔር ያሰበው፥ በልቡም ያኖረው አይደለምን? 22እግዚአብሔርም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኵሰት ይታገሥ ዘንድ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ፥ በረሃና መረገሚያ ሆናለች፤ እስከ ዛሬም የሚኖርባት የለም። 23ስላጠናችሁት ዕጣን፥ በእግዚአብሔርም ላይ ስለ በደላችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዐቱም፥ በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደ ሆነ ይች ክፉ ነገር አግኝታችኋለች።”
24ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ፥ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፥ “በግብፅ ምድር የምትኖሩ አይሁድ ሁሉ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፦ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ፥ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ የተሳልነውን ስእለታችንን በርግጥ እንፈጽማለን አላችሁ፤ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ፤ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። 26ስለዚህ እናንተ በግብፅ ምድር የምትኖሩ አይሁድ ሁሉ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ በታላቁ ስሜ ምያለሁ፥” ይላል እግዚእብሔር። 27እነሆ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት እተጋባቸዋለሁ፤ በግብፅም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ። 28ከሰይፍም የሚያመልጡ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች ከግብፅ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ ሊቀመጡም ወደ ግብፅ ምድር የገቡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንዲጸና ያውቃሉ።
29“ቃሌም በላያችሁ ለክፋት እንዲጸና ታውቁ ዘንድ በዚች ስፍራ በክፉ እንደምጐበኛችሁ ምልክታችሁ ይህ ነው፥” ይላል እግዚአብሔር። 30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው፥ ነፍሱንም ለፈለገው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ እነሆ የግብፅን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ፥ ነፍሱንም ለሚፈልጉ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።#ምዕ. 44 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 51 ከቍ. 1 እስከ 30 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 44: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ