ትንቢተ ኤርምያስ 39
39
የኢየሩሳሌም አወዳደቅ
1እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመተ መንግሥት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት። 2በሴዴቅያስም በዐሥራ አንደኛው ዓመተ መንግሥት በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን ከተማዪቱ ተለያየች። 3የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ማርጋናሳር፥ ሳማጎት፥ ናቡሳኮር፥ ናቡሰሪስ፥ ናግራጎስናሴር፥ ረብማግ፥ ኔርጋል ሴሪአጼር፥ ከቀሩት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ።
4የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ሰልፈኞቹም ሁሉ በአዩአቸው ጊዜ፥ በሌሊት ሸሹ፤ በንጉሡም አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥር መካከል በነበረው ደጅ ከከተማዪቱ ወጡ፤ በዓረባም መንገድ ወጡ። 5የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፤ ሴዴቅያስንም በኢያሪኮ ሜዳ አገኙት፤ ይዘውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ዴብላታ#ዕብ. “ሬብላ” ይላል። ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 6የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በዐይኑ ፊት በዴብላታ#ዕብ. “ሬብላ” ይላል። ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን ታላላቆች ሁሉ ገደለ። 7የሴዴቅያስንም ዐይን አወጣ፤ በሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው። 8ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። 9የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳንም በከተማዪቱ የቀሩትን ሕዝብ፥ ኰብልለውም ወደ እርሱ የገቡትን ሰዎችና የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው። 10የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳን ግን አንዳች ከሌላቸው ከሕዝቡ ድሆች ከፊሎቹን በይሁዳ ሀገር ተዋቸው፤ የወይኑን ቦታና እርሻውንም በዚያ ጊዜ ሰጣቸው።
ኤርምያስ እንደ ተፈታ
11የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳንን ስለ ኤርምያስ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ 12“ውሰደውና በመልካም ተመልከተው፤ የሚልህንም ነገር አድርግለት እንጂ ክፉን ነገር አታድርግበት።” 13የአዛዞች አለቃ ናቡዛርዳንም ላከ፤ ናቡሻዝባንም፥ ራፋስቂስም፥ ኔርጋል ሴራአጼርም፥ ራብማግም፥ የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ ላኩ።#ምዕ. 39 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 46 ሲሆን ከቍ. 4 እስከ 13 የለውም። 14ኤርምያስንም ከግዞት ቤቱ አደባባይ አወጡት፤ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እንዲህም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
ለአቤሜሌክ የተሰጠ ተስፋ
15በግዞት ቤቱ አደባባይም ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 16“ሂድ ለኢትዮጵያዊው ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ #“እነሆ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚች ከተማ ላይ አመጣለሁ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። 17በዚያም ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከፊታቸውም የተነሣ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። 18ፈጽሜ አድንሃለሁ፤ ሰውነትህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፤ በእኔ ታምነሃልና፥” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 39: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ