ትንቢተ ኤርምያስ 38
38
1ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል የተናገረውን ቃል የናታን ልጅ ሰፋንያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር#“የመልክያም ልጅ ጳስኮር” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሰሙ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን የሚወጣ ግን በሕይወት ይኖራል፤ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፤ በሕይወትም ይኖራል። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በርግጥ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።” 4አለቆቹም ንጉሡን፥ “ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚያች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ፥ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው ይገደል፤ ለዚህ ሕዝብ ክፋትን እንጂ ሰላምን አይመኝለትምና” አሉት። 5ንጉሡም ሴዴቅያስ፥ “ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ በእጃችሁ ነው” አለ። 6ኤርምያስንም ወሰዱት፤ በግዞት ቤትም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓዱም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ።
7በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “አቤድሜሌክ” ይላል። ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። 8ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ነገረው፥ 9“ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!#ግሪክ ሰባ. ሊ. ንጉሡ ክፉ አድራጊ እንደሆነ ይናገራል። እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በአደረጉት ሁሉ ክፉ አድርገዋል፤ በከተማዪቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።” 10ንጉሡም ኢትዮጵያዊዉን አቤሜሌክን፥ “ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፤ ነቢዩ ኤርምያስም ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው። 11አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፤ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፤ ከዚያም ዕላቂ ጨርቅና አሮጌ ገመድ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጕድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደው። 12ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፥ “እነዚህን ጨርቆች በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። 13ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት፤ ከጕድጓድም አወጡት፤ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
14ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን፥ “አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው። 15ኤርምያስም ንጉሡን ሴዴቅያስን፥ “ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም” አለው። 16ንጉሡም ሴዴቅያስ፥ “ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፤ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም” ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ።
17ኤርምያስም ሴዴቅያስን፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች፤ ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም፥ ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ አንተም ከእጃቸው አታመልጥም” አለው። 19ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፥ “ወደ ከለዳውያን በኰበለሉ በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል፤ እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። 20ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ለአንተም ይሻልሃል፤ ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። 21ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው። 22እነሆ በይሁዳ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች፦ ባለሟሎችህ አታልለውሃል፤ አሸንፈውህማል፤ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ። 23ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።”
24ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “ይህን ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። 25አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው፦ ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን፤ አትሸሽገንም፤ እኛም አንገድልህም፤ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ 26አንተ በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ” በላቸው። 27አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፤ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ። 28ኤርምያስም ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤቱ አደባባይ ተቀመጠ።#ምዕ. 38 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 45 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 38: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ