ትንቢተ ኤርምያስ 32
32
ኤርምያስ የእርሻ መሬት እንደ ገዛ
1በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዐሥረኛው ዓመተ መንግሥት፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በዐሥራ ስምንተኛው ዓመተ መንግሥት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2በዚያ ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። 3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አስጠብቆት ነበርና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ይቺን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል ብለህ ስለምን ትንቢት ትናገራለህ? 4የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፤ አፍ ለአፍም ይናገረዋል፤ ዐይን ለዐይንም ይተያያሉ እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ 5ሴዴቅያስም ወደ ባቢሎን ይገባል፤ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከከለዳውያን ጋር ብቷጉ ምንም አይቀናችሁም።”#“እስክጐበኘውም ድረስ በዚያ ይኖራል ከከለዳውያንም ጋር ብቷጉ አይቀናችሁም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
6የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7“እነሆ የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፦ ትገዛው ዘንድ የመቤዠቱ መብት የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ” ይልሃል። 8እንደ እግዚአብሔርም ቃል የአጎቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወደ አለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ፥ “በብንያም ሀገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ፤ የመግዛትና የመውረስ#“የመውረስ” የሚለው በግእዝ ብቻ። መብቱ የአንተ ነውና፥ አንተ ታላቃችን ነህና፤ ለአንተ ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ዐወቅሁ። 9በዐናቶትም ያለውን እርሻ ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። 10የውሉንም ወረቀት ጻፍሁ፤ አተምሁትም፤ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። 11የታተመውንም የውል ወረቀት ወሰድሁ፤ 12የአጎቴም ልጅ አናምኤል፥ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፥ በግዞት ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድም ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለማሴው ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። 13በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት፦ 14“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብዙ ቀን ይጠበቅ ዘንድ የታተመውን ይህን የውል ወረቀት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑረው። 15የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህ ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።”
የኤርምያስ ጸሎት
16ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፦ 17“ወዮ! አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ ከአንተም የሚሳን ምንም ነገር የለም። 18ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ! ለብዙ ሺህ ምሕረትን ታደርጋለህ፤ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ። 19እግዚአብሔር በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ስምህ ታላቅ የሆነ፥ ኀያል፥ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዐይኖችህ በሰው ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። 20እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብፅ ምድር፥ ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፤ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል። 21በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ ምድር አወጣህ። 22ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርም የምታፈስሰውን ምድር ሰጠሃቸው፤ 23እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም፤ በሕግህም አልሄዱም፤ ያደርጉም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። 24አሕዛብም መጥተው ይህችን ሀገር ያዟት፤ ይህችም ከተማ ከረኃቡና ከጦሩ የተነሣ በወጓት በከለዳውያን ሰዎች እጅ ወደቀች፤ እንደ ተናገርኸውም ሆነ።#በዕብራይስጥ ይለያል። 25አንተም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እርሻውን በብር ግዛ፤ ምስክሮችንም ጥራ አልኸኝ፤ እኔም ውሉን ጽፌ አተምሁ፤ ምስክሮችንም አቆምሁ፤#“እኔም ውሉን ጽፌ አተምሁ ፤ ምስክሮችንም አቆምሁ” የሚለው በዕብ. የለም። ከተማዪቱ ግን ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች።”
26የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27“እነሆ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ ከእኔ የሚሰወር ነገር አለን? 28ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ይችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል። 29ይችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን ይመጣሉ፤ ከተማዋንም በእሳት ያነድዱአታል፤ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበዓል ያጠኑባቸውን፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸውን ቤቶች ያቃጥሉአቸዋል። 30የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና፥#“የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደርጉምና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ይላል እግዚአብሔር። 31ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በቁጣዬና በመዓቴ ውስጥ ናትና፤#ዕብ. “ቍጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና” ይላል። 32ይህም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው፥ አለቆቻቸውም፥ ካህናቶቻቸውም፥ ነቢያቶቻቸውም፥ የይሁዳም ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ስለ አደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። 33ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳስተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም። 34ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኵሰታቸውን አኖሩ። 35ይሁዳን ወደ ኀጢአት እንዲያገቡት፥ ይህን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ፥ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን መሠዊያዎች ለበዓል ሠሩ።”
አስተማማኝ ተስፋ
36አሁን እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አንተ ስለ እርስዋ፥ “በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል፦ 37እነሆ በቍጣዬና በመዓቴ፥ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት ሀገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ 38እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39ለእነርሱም፥ ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘለዓለም እንዲፈሩኝ ሌላ #ዕብ. “አንድ” ይላል። መንገድና ሌላ#ዕብ. “አንድ” ይላል። ልብ እሰጣቸዋለሁ። 40ከእነርሱም እንዳልመለስ፥ ከእነርሱ ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ይቅር እላቸዋለሁ፤ በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። 42እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። 43እናንተም፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት፤ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን እንደ ገና ይገዛሉ። 44ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም ሀገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች፥ በቆላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ፤ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ፤ ምስክሮችንም ያቆማሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።#ምዕ. 32 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 39 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 32: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ