ስለ ነቢያት ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፤ አጥንቶችም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ፤ ከጌትነቱም ክብር የተነሣ እኔም በመከራ እንደ ተቀጠቀጠ ሰው፥ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈውም እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። ዝሙታቸው ምድርን ሞልትዋልና፥ ከመርገም ፊት የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ ማሰሪያው ሁሉ ደርቆአል፤ ሥራቸውና ድካማቸው ከንቱ ሆነ። “ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ መንገዳቸው ድጥና ጨለማ ትሆንባቸዋለች፤ እነርሱም ፍግምግም ብለው ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር። በበዓል ትንቢት የተናገሩበትን የሰማርያን ነቢያት ኀጢአታቸውን አይቻለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አሳትዋቸው። በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም፥ የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና ሕማምን አበላቸዋለሁ፤ መራራ ውኃንም አጠጣቸዋለሁ።” ኀያል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ለሚያቃልሉ ሰላም ይሆንላችኋል፥ በፍላጎታቸውና በልቡናቸው ክፋት ለሚሄዱም ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም” ይላሉ። በእግዚአብሔር ምክር የሚቆም፥ ቃሉን የሚያይና የሚሰማ ማን ነው? ቃሉንስ ያዳመጠ፥ የሰማስ ማንነው? እነሆ ከእግዚአብሔር ዘንድ ንውጽውጽታ ይመጣል፤ ኃጥኣንን ያነዋውጣቸውና ይገለብጣቸው ዘንድ መቅሠፍት ይመጣባቸዋል፤ የዐመፀኞችን ራስ ይገለባብጣል። የእግዚአብሔር ቍጣ የልቡን ዐሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛውም ዘመን ያውቁታል። “እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። በቃሌ ቢቆሙና ምክሬን ቢሰሙ ኖሮ ግን ሕዝቤን ከክፉ ሥራቸው በመለሱአቸው ነበር። “እኔ ቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ ሩቅ አምላክ አይደለሁም ይላል እግዚአብሔር። ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር። ሕልምን አለምን እያሉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? አባቶቻቸው ስለ በዓል ስሜን እንደ ረሱ፥ እያንዳንዱ ለባልንጀራው በሚናገራት ሕልማቸው ሕዝቤን ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? ይላል እግዚአብሔር። በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እነሆ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው፦ እርሱ የእግዚአብሔር ሸክም ነው በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እነሆ ሐሰትን በሚያልሙ፥ በሚናገሩም፥ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውምም፤ ለእነዚህ ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም፥” ይላል እግዚአብሔር። ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፥ “የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው?” ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፥ “ሸክሙ እናንተ ናችሁ፤ እጥላችሁማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር” ትላቸዋለህ። የእግዚአብሔር ሸክም የሚለውን ነቢይንና ካህንን፥ ሕዝብንም ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። አንዱም አንዱ ለባልንጀራው፥ አንዱም አንዱ ለወንድሙ እንዲህ ይበል፥ “እግዚአብሔር የመለሰው ምንድን ነው? እግዚአብሔርስ ምን ነገር ተናገረ?” ለሰው ሁሉ ቃሉ ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን የሕያውን አምላክ ቃል ለውጣችኋልና። ለነቢዩ፥ “እግዚአብሔር ምን መለሰልህ እግዚአብሔርስ የተናገረው ምንድን ነው?” በሉ ምን ተናገረ? ነገር ግን፥ “የእግዚአብሔር ሸክም” ብትሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እኔ፦ የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል፦ የእግዚአብሔር ሸክም ብላችኋልና፥ ስለዚህ፥ እነሆ- ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ አንሥቼ እጥላለሁ። የዘለዓለምንም ስድብና ከቶ ተረስቶ የማይጠፋውን የዘለዓለምን ውርደት አመጣባችኋለሁ።”
ትንቢተ ኤርምያስ 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 23:9-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች