የከነዓናውያንንም ጦርነት ሁሉ ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ተዋቸው። ይህም ጦርነትን ያስተምሩአቸው ዘንድ ስለ እስራኤል ልጆች ትውልድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ከእነርሱ በፊት የነበሩት እነዚህን አላወቋቸውም ነበር፤ እነርሱም አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበዓልሄርሞን ተራራ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዌዎናውያን፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ። የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን፥ በኬጤዎናውያን፥ በአሞሬዎናውያን፥ በፌርዜዎናውያን፥ በኤዌዎናውያን፥ በኢያቡሴዎናውያንም መካከል ተቀመጡ። ሴቶች ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፤ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረጉ፤ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በዓሊምንና አስታሮትን አመለኩ። ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ በወንዞችም መካከል ባለች በሶርያ ንጉሥ በኩሳርሳቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኩሳርሳቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል መድኀኒትን አስነሣላቸው። የካሌብ የታናሽ ወንድሙ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልም አዳናቸው፤ ለእርሱም ታዘዙለት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለጦርነትም ወጣ፤ እግዚአብሔርም በወንዞች መካከል ያለች የሶርያ ንጉሥ ኩሳርሳቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኩሳርሳቴም ላይ በረታች። ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው። የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፤ ዘንባባ ያለባትንም ከተማ ያዘ። የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም ዐሥራ ስምንት ዓመት ተገዙ። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ሁለቱ እጆቹ ቀኝ የሆኑለትን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም እጅ መንሻ ላኩ። ናዖድም ሁለት አፍ ያላት ርዝመቷ አንድ ስንዝር የሆነች ሰይፍ አበጀ፤ ከልብሱም በታች በቀኝ በኩል በወገቡ ታጠቃት። ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም እጅ መንሻውን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ። እጅ መንሻውንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ እጅ መንሻ የተሸከሙትን ሰዎች አሰናበታቸው። ዔግሎምም ከገልገል ከጣዖታቱ ቤት ተመለሰ። ናዖድም፥ “ንጉሥ ሆይ፥ ለብቻህ የምነግርህ የምሥጢር ነገር አለኝ” አለ፤ ዔግሎምም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ እንዲወጣ አዘዘ፤ በእርሱም ዘንድ የቆሙት ሁሉ ወጡ ። ናዖድም ወደ እርሱ ገባ፤ እርሱም በበጋ ቤቱ ሰገነት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም፥ “ንጉሥ ሆይ! የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ” አለው። ዔግሎምም ከዙፋኑ ተነሣ፥ ቀረበውም። ናዖድም በተነሣ ጊዜ ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጎኑ ሰይፉን መዘዘ፤ ዔግሎምንም ሆዱን ወጋው፤ እስከ ውላጋዋም አስገባት፤ እስከ ጀርባውም በረበረው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣትም። ናዖድም የእልፍኙን ደጅ ዘግቶና ቈልፎ ወደ ውጭ ወጣ። ናዖድም ከሄደ በኋላ አገልጋዮቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ፥ “ምናልባት በበጋ ሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል” አሉ። እስኪያፍሩም ድረስ ቈዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፤ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ላይ ወድቆ ሞቶም አገኙት። እስከሚታወኩም ድረስ ናዖድ አመለጠ፤ ያወቀውም የለም፤ ከጣዖቶቻቸውም አልፎ ወደ ሴይሮታ አመለጠ። ከዚህም በኋላ ወደ እስራኤል ምድር በደረሰ ጊዜ በተራራማው በኤፍራም ሀገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው ሀገር ወረዱ፤ እርሱም በፊታቸው ሄደ።
መጽሐፈ መሳፍንት 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 3:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች