በከነዓን ምድር ጦርነት ያልተለማመዱ እስራኤላውያንን ለመፈተን እግዚአብሔር በምድሪቱ የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህንንም ማድረጉ ቀድሞ የጦርነት ልምድ ያልነበራቸውን የእስራኤልን ትውልድ የጦርነት ስልት ለማስተማር ብሎ ብቻ ነው። በምድሪቱ ላይ የቀሩትም፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መሪዎች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከባዓልሔርሞን ተራራ አንሥቶ እስከ ሐማት ድረስ በሊባኖስ ተራራዎች የሚኖሩት ሒዋውያን ነበሩ። እነርሱም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደ ሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በከነዓናውያን፥ በሒታውያን፥ በአሞራውያን፥ በፈሪዛውያን፥ በሒዋውያንና በኢያቡሳውያን መካከል ኖሩ። የእነርሱን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፤ አማልክታቸውንም አመለኩ። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን እግዚአብሔርንም ትተው በዓልና አሼራን አመለኩ፤ ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ነደደ፤ ለመስጴጦምያው ንጉሥ ለኩሻን ፊሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለኩሻን ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት ተገዙለት፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነውን የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን አስነሣቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሻን ፊሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሻን ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። በምድሪቱም ላይ ለአርባ ዓመት ያኽል ሰላም ሰፍኖ ከቈየ በኋላ የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ሞተ። የእስራኤል ሕዝብ እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የሞአቡን ንጉሥ ዔግሎንን ከእስራኤል ይበልጥ የበረታ እንዲሆን አደረገው። ዔግሎንም ዐሞናውያንንና ዐማሌቃውያንን አስተባብሮ እስራኤልን ወጋ፤ የተምር ዛፍ የሞላባትንም የኢያሪኮን ከተማ በቊጥጥራቸው ሥር አደረጉ። የእስራኤል ሕዝብ ለዐሥራ ስምንት ዓመት ለሞአብ ንጉሥ ለዔግሎን ተገዢዎች ሆኑ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ ግራኝ የነበረውን የጌራን ልጅ ኤሁድን አዳኝ አድርጎ አስነሣቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ኤሁድን ግብር አስይዘው ወደ ሞአብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት። ኤሁድ ኀምሳ ሳንቲ ሜትር የሚያኽል ርዝመት ያለው በሁለት በኩል ስለ ታም የሆነ ሰይፍ ለራሱ አሠራ፤ እርሱንም በቀኝ ጭኑ በኩል በልብሱ ውስጥ ታጠቀው፤ ከዚያን በኋላ ሰውነቱ በጣም ወፍራም ለነበረው ለዔግሎን ግብሩን ይዞ ሄደ። ኤሁድ ግብሩን ለንጉሡ ካቀረበ በኋላ ግብሩን ተሸክመው የነበሩትን ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ፤ ኤሁድ ራሱ ግን በጌልገላ አጠገብ ወዳሉት ተጠርበው ወደ ተተከሉ የጣዖት ድንጋዮች ዞር ብሎ ቈየ፤ ወደ ዔግሎንም ተመልሶ “ንጉሥ ሆይ! በግል ለአንተ የምነግርህ አንድ ምሥጢር አለኝ” አለው። እርሱም “ዝም በል” አለው። ስለዚህም ንጉሡ ባለሟሎቹን “እስቲ አንድ ጊዜ ውጪ ቈዩልን!” አላቸው፥ እነርሱም በሙሉ ወጡ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በጣራው ላይ ባለው ነፋሻ ክፍል ለብቻው ተቀምጦ ሳለ፥ ኤሁድ ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ “ከእግዚአብሔር ለአንተ የተላከ መልእክት አለኝ” አለው፤ ንጉሡም ብድግ ብሎ ቆመ። ኤሁድም ሰይፉን ከቀኝ ጭኑ በግራ እጁ መዞ በንጉሡ ሆድ ውስጥ ሻጠ፤ እጀታው ሳይቀር ሰይፉ በሙሉ ወደ ሆድ ዕቃው ገባ፤ እስከ ጀርባውም ዘለቀ፤ ሞራውም ሰይፉን ሸፈነው፤ ኤሁድም ሰይፉን ከንጉሡ ሆድ አላወጣውም። ከዚያን በኋላ ኤሁድ ወደ ውጪ ወጣ፤ በሮቹንም ዘግቶ ቈለፈበት። ኤሁድ ከሄደ በኋላ የንጉሡ አገልጋዮች መጥተው በሮቹ እንደ ተቈለፉ አዩ፤ ነገር ግን ንጉሡ ከውስጥ በኩል በመጸዳዳት የዘገየ መሰላቸው፤ መቈየት የሚገባቸውን ያኽል በውጪ ቈዩ፤ ነገር ግን አሁንም በሩ እንዳልተከፈተ ባዩ ጊዜ ቊልፉን ወስደው በሩን ከፈቱ፤ እዚያም ጌታቸው ሞቶ በወለል ላይ መዘርጋቱን ተመለከቱ። እነርሱ እዚያው ቆመው በሚጠባበቁበት ጊዜ ኤሁድ ርቆ ሄዶ ነበር፤ ተጠርበው የተተከሉ የጣዖት ድንጋዮችን አልፎ ወደ ሰዒራ አመለጠ፤ እዚያም ወደ ኮረብታማው ወደ ኤፍሬም አገር እንደ ደረሰ በኤፍሬም ተራራማው አገር የክተት እምቢልታ ነፋ፤ የእስራኤልም ሕዝብ በእርሱ መሪነት ተከትለውት ወረዱ።
መጽሐፈ መሳፍንት 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 3:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች