ከዚህ በኋላ በሶሬሕ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ። የፍልስጥኤማውያን መሳፍንትም ወደ እርስዋ ወጥተው፥ “እርሱን አባብለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኀይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛም እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ ዕወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን” አሉአት። ደሊላም ሶምሶንን፥ “ታላቅ ኀይልህ በምን እንደ ሆነ፥ በምንስ ብትታሰር እንደምትዋረድ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሶምሶንም፥ “በሰባት ባልደረቀ በርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ” አላት ። የፍልስጥኤማውያን መሳፍንትም ሰባት ያልደረቀ ርጥብ ጠፍር አመጡላት፤ በእነርሱም አሰረችው። የሚያደቡትም ሰዎች በጓዳዋ ውስጥ ተደብቀው ነበር። እርስዋም፥ “ሶምሶን ሆይ! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱም ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፤ ኀይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም። ደሊላም ሶምሶንን፥ “እነሆ፥ አታለልኸኝ፤ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደሆነ፥ እባክህ ንገረኝ” አለችው። እርሱም፥ “ሥራ ባልተሠራባቸው ሰባት አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላውም ሰው እሆናለሁ” አላት። ደሊላም ሰባት አዳዲስ ገመዶች ወስዳ በእነርሱ አሰረችው፤ የሚያደቡትም ሰዎች በጓዳዋ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። እርስዋም፥ “ሶምሶን ሆይ! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ገመዶችንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሳቸው። ደሊላም ሶምሶንን፥ “እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፤ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ የምትታሰርበት ምን እንደሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም፥ “የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ብትጐነጕኚው፥ በግድግዳም ላይ በችካል ብትቸክዪው፥ ከሰዎች እንደ አንዱ እደክማለሁ፥” አላት። ደሊላም አስተኛችው፤ የራሱንም ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤ በግድግዳም ላይ በችካል ቸከለቻቸው፥ “ሶምሶን ሆይ! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፥ ችካሉንም ከነቈንዳላው ከግድግዳው ነቀለ፤ ኀይሉም አልታወቀም። ደሊላም፥ “ ‘አንተ እወድድሻለሁ’ እንዴት ትለኛለህ? ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም፤ ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኀይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም” አለችው። ከዚህም በኋላ ሌሊቱን ሁሉ በነገር በዘበዘበችውና በአደከመችው ጊዜ፥ ልሙት እስኪል ድረስ ተበሳጨ። እርሱም፥ “ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር ናዝራዊ ነኝና ራሴን ምላጭ አልነካኝም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኀይሌ ከእኔ ይነሣል፤ እደክማለሁም፤ እንደ ሌላም ሰው ሁሉ እሆናለሁ” ብሎ የልቡን ሁሉ ነገራት። ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ነገራት ባወቀች ጊዜ፥ “የልቡን ሁሉ ነግሮኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ” ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መሳፍንት ጠራች። የፍልስጥኤማውያንም መሳፍንት ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ። እርስዋም በጕልበቷ ላይ አስተኛችው፤ ጠጕር ቈራጭም ጠራች፤ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ይደክምም ጀመረ፤ ኀይሉም ከእርሱ ሄደ። ደሊላም፥ “ሶምሶን ሆይ! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ፥ “እወጣለሁ፤ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ፤ አጠፋቸዋለሁም” አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም። ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዐይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አውርደው በእግር ብረት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። የራሱም ጠጕር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር። የፍልስጥኤም መሳፍንትም፥ “አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ፥ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ፥ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ። ከዚህም በኋላ ልባቸውን ደስ ባለው ጊዜ፥ “በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ከእስር ቤት ጥሩት” አሉ። ሶምሶንንም ከእስር ቤት ጠሩት፤ በፊታቸውም ተጫወተ፤ ተዘባበቱበትም፤ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት። ሶምሶንም የሚመራውን ብላቴና፥ “ቤቱን የደገፉትን ምሰሶዎች እደገፍባቸው ዘንድ እባክህ አስይዘኝ” አለው፥ ብላቴናውም እንዳለው አደረገለት። በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፤ የፍልስጥኤም መሳፍንትም ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። ሶምሶንም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ ጌታዬ ሆይ! አስበኝ፤ ጌታዬ ሆይ! አንድ ጊዜ አበርታኝ፤ እንግዲህ ስለ ሁለቱ ዐይኖቼ ፋንታ ከፍልስጥኤማውያን አንዲት በቀልን እበቀላለሁ።” ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶዎች ያዘ፤ አንዱን በቀኝ እጁ፥ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ገፋቸው። ሶምሶንም፥ “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ነፍሴ ትውጣ” አለ፤ ተጎንብሶም ምሰሶዎቹን በሙሉ ኀይሉ ገፋቸው፤ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመሳፍንቱ፥ በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወቱ ሳለ ከገደላቸው በዙ። ወንድሞቹም፥ የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፤ ይዘውም አመጡት፤ በሶሬሕና በኢስታሔል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት። እርሱም እስራኤልን ሃያ ዓመት ገዛቸው።
መጽሐፈ መሳፍንት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 16:4-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች