መሳፍንት 16:4-31

መሳፍንት 16:4-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚህ በኋላ በሶ​ሬሕ ሸለቆ የነ​በ​ረች ደሊላ የተ​ባ​ለች አን​ዲት ሴትን ወደደ። የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መሳ​ፍ​ን​ትም ወደ እር​ስዋ ወጥ​ተው፥ “እር​ሱን አባ​ብ​ለሽ በእ​ርሱ ያለ ታላቅ ኀይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛም እር​ሱን ለማ​ዋ​ረድ እና​ስ​ረው ዘንድ የም​ና​ሸ​ን​ፈው በምን እንደ ሆነ ዕወቂ፤ እኛም እያ​ን​ዳ​ን​ዳ​ችን ሺህ አንድ መቶ ብር እን​ሰ​ጥ​ሻ​ለን” አሉ​አት። ደሊ​ላም ሶም​ሶ​ንን፥ “ታላቅ ኀይ​ልህ በምን እንደ ሆነ፥ በም​ንስ ብት​ታ​ሰር እን​ደ​ምትዋ​ረድ እባ​ክህ ንገ​ረኝ” አለ​ችው። ሶም​ሶ​ንም፥ “በሰ​ባት ባል​ደ​ረቀ በር​ጥብ ጠፍር ቢያ​ስ​ሩኝ፥ እደ​ክ​ማ​ለሁ፤ እንደ ሌላም ሰው እሆ​ና​ለሁ” አላት ። የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መሳ​ፍ​ን​ትም ሰባት ያል​ደ​ረቀ ርጥብ ጠፍር አመ​ጡ​ላት፤ በእ​ነ​ር​ሱም አሰ​ረ​ችው። የሚ​ያ​ደ​ቡ​ትም ሰዎች በጓ​ዳዋ ውስጥ ተደ​ብ​ቀው ነበር። እር​ስ​ዋም፥ “ሶም​ሶን ሆይ! ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መጡ​ብህ” አለ​ችው። እር​ሱም ፈትል እሳት በሸ​ተ​ተው ጊዜ እን​ዲ​በ​ጠስ ጠፍ​ሩን በጣ​ጠ​ሰው፤ ኀይ​ሉም በምን እንደ ሆነ አል​ታ​ወ​ቀም። ደሊ​ላም ሶም​ሶ​ንን፥ “እነሆ፥ አታ​ለ​ል​ኸኝ፤ የነ​ገ​ር​ኸ​ኝም ሐሰት ነው፤ አሁ​ንም የም​ት​ታ​ሰ​ር​በት ምን እን​ደ​ሆነ፥ እባ​ክህ ንገ​ረኝ” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “ሥራ ባል​ተ​ሠ​ራ​ባ​ቸው ሰባት አዳ​ዲስ ገመ​ዶች ቢያ​ስ​ሩኝ፥ እደ​ክ​ማ​ለሁ፤ እንደ ሌላ​ውም ሰው እሆ​ና​ለሁ” አላት። ደሊ​ላም ሰባት አዳ​ዲስ ገመ​ዶች ወስዳ በእ​ነ​ርሱ አሰ​ረ​ችው፤ የሚ​ያ​ደ​ቡ​ትም ሰዎች በጓ​ዳዋ ውስጥ ተቀ​ም​ጠው ነበር። እር​ስ​ዋም፥ “ሶም​ሶን ሆይ! ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መጡ​ብህ” አለ​ችው። ገመ​ዶ​ች​ንም ከክ​ንዱ እንደ ፈትል በጣ​ጠ​ሳ​ቸው። ደሊ​ላም ሶም​ሶ​ንን፥ “እስከ አሁን ድረስ አታ​ለ​ል​ኸኝ፤ የነ​ገ​ር​ኸ​ኝም ሐሰት ነው፤ የም​ት​ታ​ሰ​ር​በት ምን እን​ደ​ሆነ ንገ​ረኝ” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “የራ​ሴን ጠጕር ሰባ​ቱን ጕን​ጕን ከድር ጋር ብት​ጐ​ነ​ጕ​ኚው፥ በግ​ድ​ግ​ዳም ላይ በች​ካል ብት​ቸ​ክ​ዪው፥ ከሰ​ዎች እንደ አንዱ እደ​ክ​ማ​ለሁ፥” አላት። ደሊ​ላም አስ​ተ​ኛ​ችው፤ የራ​ሱ​ንም ጠጕር ሰባ​ቱን ጕን​ጕን ከድር ጋር ጐነ​ጐ​ነ​ችው፤ በግ​ድ​ግ​ዳም ላይ በች​ካል ቸከ​ለ​ቻ​ቸው፥ “ሶም​ሶን ሆይ! ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መጡ​ብህ” አለ​ችው። ከእ​ን​ቅ​ል​ፉም ነቃ፥ ችካ​ሉ​ንም ከነ​ቈ​ን​ዳ​ላው ከግ​ድ​ግ​ዳው ነቀለ፤ ኀይ​ሉም አል​ታ​ወ​ቀም። ደሊ​ላም፥ “ ‘አንተ እወ​ድ​ድ​ሻ​ለሁ’ እን​ዴት ትለ​ኛ​ለህ? ልብህ ከእኔ ጋር አይ​ደ​ለም፤ ስታ​ታ​ል​ለኝ ይህ ሦስ​ተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኀይ​ል​ህም በምን እንደ ሆነ አል​ነ​ገ​ር​ኸ​ኝም” አለ​ችው። ከዚ​ህም በኋላ ሌሊ​ቱን ሁሉ በነ​ገር በዘ​በ​ዘ​በ​ች​ውና በአ​ደ​ከ​መ​ችው ጊዜ፥ ልሙት እስ​ኪል ድረስ ተበ​ሳጨ። እር​ሱም፥ “ከእ​ናቴ ማኅ​ፀን ጀምሬ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ናዝ​ራዊ ነኝና ራሴን ምላጭ አል​ነ​ካ​ኝም፤ የራ​ሴ​ንም ጠጕር ብላጭ ኀይሌ ከእኔ ይነ​ሣል፤ እደ​ክ​ማ​ለ​ሁም፤ እንደ ሌላም ሰው ሁሉ እሆ​ና​ለሁ” ብሎ የል​ቡን ሁሉ ነገ​ራት። ደሊ​ላም የል​ቡን ሁሉ እንደ ነገ​ራት ባወ​ቀች ጊዜ፥ “የል​ቡን ሁሉ ነግ​ሮ​ኛ​ልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ” ብላ ላከ​ችና የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን መሳ​ፍ​ንት ጠራች። የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም መሳ​ፍ​ንት ብሩን በእ​ጃ​ቸው ይዘው ወደ እር​ስዋ መጡ። እር​ስ​ዋም በጕ​ል​በቷ ላይ አስ​ተ​ኛ​ችው፤ ጠጕር ቈራ​ጭም ጠራች፤ እር​ሱም ሰባ​ቱን የራ​ሱን ጕን​ጕን ላጨው። ይደ​ክ​ምም ጀመረ፤ ኀይ​ሉም ከእ​ርሱ ሄደ። ደሊ​ላም፥ “ሶም​ሶን ሆይ! ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን መጡ​ብህ” አለ​ችው። ከእ​ን​ቅ​ል​ፉም ነቅቶ፥ “እወ​ጣ​ለሁ፤ እንደ ወት​ሮ​ውም ጊዜ አደ​ር​ጋ​ለሁ፤ አጠ​ፋ​ቸ​ዋ​ለ​ሁም” አለ። ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእ​ርሱ እንደ ተለ​የው አላ​ወ​ቀም። ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ይዘው ዐይ​ኖ​ቹን አወ​ጡት፤ ወደ ጋዛም አው​ር​ደው በእ​ግር ብረት አሰ​ሩት፤ በግ​ዞ​ትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። የራ​ሱም ጠጕር ከላ​ጩት በኋላ ያድግ ጀመር። የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤም መሳ​ፍ​ን​ትም፥ “አም​ላ​ካ​ችን ጠላ​ታ​ች​ንን ሶም​ሶ​ንን በእ​ጃ​ችን አሳ​ልፎ ሰጠን” እያሉ ለአ​ም​ላ​ካ​ቸው ለዳ​ጎን ታላቅ መሥ​ዋ​ዕት ይሠዉ ዘንድ፥ ደስም ይላ​ቸው ዘንድ ተሰ​በ​ሰቡ። ሕዝ​ቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ፥ “ምድ​ራ​ች​ንን ያጠ​ፋ​ውን፥ ከእ​ኛም ብዙ ሰው የገ​ደ​ለ​ውን ጠላ​ታ​ች​ንን አም​ላ​ካ​ችን በእ​ጃ​ችን አሳ​ልፎ ሰጠን እያሉ አም​ላ​ካ​ቸ​ውን አመ​ሰ​ገኑ። ከዚ​ህም በኋላ ልባ​ቸ​ውን ደስ ባለው ጊዜ፥ “በፊ​ታ​ችን እን​ዲ​ጫ​ወት ሶም​ሶ​ንን ከእ​ስር ቤት ጥሩት” አሉ። ሶም​ሶ​ን​ንም ከእ​ስር ቤት ጠሩት፤ በፊ​ታ​ቸ​ውም ተጫ​ወተ፤ ተዘ​ባ​በ​ቱ​በ​ትም፤ በም​ሰ​ሶና በም​ሰ​ሶም መካ​ከል አቆ​ሙት። ሶም​ሶ​ንም የሚ​መ​ራ​ውን ብላ​ቴና፥ “ቤቱን የደ​ገ​ፉ​ትን ምሰ​ሶ​ዎች እደ​ገ​ፍ​ባ​ቸው ዘንድ እባ​ክህ አስ​ይ​ዘኝ” አለው፥ ብላ​ቴ​ና​ውም እን​ዳ​ለው አደ​ረ​ገ​ለት። በቤ​ትም ውስጥ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ሞል​ተ​ው​በት ነበር፤ የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤም መሳ​ፍ​ን​ትም ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤ​ቱም ሰገ​ነት ላይ ሶም​ሶን ሲጫ​ወት የሚ​ያዩ ሦስት ሺህ የሚ​ያ​ህሉ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ነበሩ። ሶም​ሶ​ንም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጮኸ፥ እን​ዲ​ህም አለ፥ “አቤቱ ጌታዬ ሆይ! አስ​በኝ፤ ጌታዬ ሆይ! አንድ ጊዜ አበ​ር​ታኝ፤ እን​ግ​ዲህ ስለ ሁለቱ ዐይ​ኖቼ ፋንታ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን አን​ዲት በቀ​ልን እበ​ቀ​ላ​ለሁ።” ሶም​ሶ​ንም ቤቱ ተደ​ግ​ፎ​ባ​ቸው የነ​በ​ሩ​ትን ሁለ​ቱን መካ​ከ​ለ​ኞች ምሰ​ሶ​ዎች ያዘ፤ አን​ዱን በቀኝ እጁ፥ አን​ዱ​ንም በግራ እጁ ይዞ ገፋ​ቸው። ሶም​ሶ​ንም፥ “ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ጋር ነፍሴ ትውጣ” አለ፤ ተጎ​ን​ብ​ሶም ምሰ​ሶ​ዎ​ቹን በሙሉ ኀይሉ ገፋ​ቸው፤ ቤቱም በው​ስጡ በነ​በ​ሩት በመ​ሳ​ፍ​ንቱ፥ በሕ​ዝ​ቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞ​ቱም የገ​ደ​ላ​ቸው ሙታን በሕ​ይ​ወቱ ሳለ ከገ​ደ​ላ​ቸው በዙ። ወን​ድ​ሞ​ቹም፥ የአ​ባቱ ቤተ ሰቦ​ችም ሁሉ ወረዱ፤ ይዘ​ውም አመ​ጡት፤ በሶ​ሬ​ሕና በኢ​ስ​ታ​ሔል መካ​ከል ባለው በአ​ባቱ በማ​ኑሄ መቃ​ብር ቀበ​ሩት። እር​ሱም እስ​ራ​ኤ​ልን ሃያ ዓመት ገዛ​ቸው።

መሳፍንት 16:4-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፣ “እርሱን አስረን በቍጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደ ሆነ እንዲያሳይሽ እስኪ አባብዪው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት። ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፣ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቍጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሳምሶንም፣ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው። ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው። ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደ ሆነ ሊታወቅ አልቻለም። ደሊላም ሳምሶንን፣ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው። እርሱም፣ “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው። ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፣ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደ ሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም መልሶ፣ “የራስ ጠጕሬን ሰባት ሹሩባዎች ከድር ጋራ ጐንጕነሽ በችካል ብትቸክዪው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ሹሩባዎቹን ከድር ጋራ ጐነጐነችው፤ ከችካልም ጋራ ቸከለችው። እንደ ገናም፣ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፣ ከነሹሩባው ነቀለው። ከዚያም፣ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኀይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው። በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው። ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንሁ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጕር ቢላጭ ግን ኀይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላ ሁሉንም ነገር እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ፣ ለፍልስጥኤማውያን ገዦች “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና ተመልሳችሁ ኑ” ብላ ላከችባቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም ብሩን ይዘው ተመልሰው መጡ። ደሊላ፣ ሳምሶንን በጭኗ ላይ አስተኝታ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገች በኋላ አንድ ሰው ጠርታ ሰባቱን የጠጕር ሹሩባዎቹን አስላጨቻቸው፤ እርሷም ታስጨንቀው ጀመር፤ ኀይሉም ተለየው። እርሷም፣ “ሳምሶን፤ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቅቶ፣ “እንደ ወትሮው አደርጋለሁ” አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ተወው አላወቀም ነበር። ከዚያም ፍልስጥኤማውያን ያዙት፤ ዐይኖቹን አውጥተው ወደ ጋዛ ይዘውት ወረዱ፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም እስር ቤት ውስጥ እህል እንዲፈጭ አደረጉት። ነገር ግን ከተላጨ በኋላ ጠጕሩ እንደ ገና ማደግ ጀመረ። በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፣ “አምላካችን ዳጎን፣ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ፣ አምላካቸውን ዳጎንን በማመስገን፣ “ምድራችንን ያጠፋውን፣ ብዙ ሰው የገደለብንን፣ ጠላታችንን፣ አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ። እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፣ “እንዲያዝናናን ሳምሶንን አምጡት” አሉ፤ ስለዚህ ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠርተው አስመጡት፤ በፊታቸውም ተጫወተ። በምሰሶዎቹ መካከል ባቆሙት ጊዜ፣ ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፣ “ቤተ ጣዖቱን ደግፈው ወደ ያዙት ምሰሶዎች አስጠጋኝና ልደገፋቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ቤተ ጣዖቱን ሞልተውት ነበር፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም በሙሉ በዚያ ነበሩ፤ ሳምሶን ሲጫወት ለማየት ሦስት ሺሕ ያህል ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ። ሳምሶንም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ። አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።” ከዚያም ቤተ ጣዖቱን መካከል ላይ ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አንዱን በቀኙ፣ አንዱን በግራ እጁ ዐቅፎ በመያዝ፣ “ከፍልስጥኤማውያን ጋራ አብሬ ልሙት” በማለት ባለ ኀይሉ ሲገፋው፣ ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው። ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤተ ሰብ ሬሳውን ለማምጣት ወደዚያ ወረዱ፤ አምጥተውም የአባቱ የማኑሄ መቃብር ባለበት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ቀበሩት። ሳምሶን በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ።

መሳፍንት 16:4-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ። የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው፦ እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፥ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት። ደሊላም ሶምሶንን፦ ታላቅ ኃይልህ በምን እንደ ሆነ፥ እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው። ሳምሶን የጌታ ባሪያ ሶምሶንም፦ በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ እንደ ሌላ ሰው እሆናለሁ አላት። የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ሰባት ያልደረቀ እርጥብ ጠፍር አመጡላት፥ በእርሱም አሰረችው። በጓዳዋም ውስጥ ሰዎች ተደብቀው ነበር። እርስዋም፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። እርሱም የተልባ እግር ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፥ ኃይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም። ደሊላም ሶምሶንን፦ እነሆ፥ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሀሰት ነው፥ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው። እርሱም፦ ሥራ ባልተሠራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት። ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ በእርሱ አሰረችው፥ በጓዳዋም የተደበቁ ሰዎች ተቀምጠው ነበር። እርስዋም፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ገመዱንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። ደሊላም ሶምሶንን፦ እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፥ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ ንገረኝ አለችው። እርሱም፦ የራሴን ጠጉር ሰባቱን ጉንጉን ከድር ጋር ብትጐነጉኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት። ሶምሶንም በተኛ ጊዜ ደሊላ የራሱን ጠጉር ሰባቱን ጉንጉን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፥ በችካልም ቸከለችውና፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፥ ችካሉንም ከነቆንዳላው ድሩንም ነቀለ። እርስዋም፦ አንተ፦ እወድድሻለሁ እንዴት ትለኛለህ፥ ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም? ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኃይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም አለችው። ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች። እርሱም፦ ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፥ የራሴንም ጠጉር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደማክለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት። ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ገለጠላት ባየች ጊዜ፦ የልቡን ሁሉ ገልጦልኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መኳንንት ጠራች። የፍልስጥኤማውያን መኳንንትም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ። እርስዋም በጉልበትዋ ላይ አስተኛችው፥ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጉንጉን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ። እርስዋም፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ፦ እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም። ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፥ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፥ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። የራሱም ጠጉር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር። የፍልስጥኤምም መኳንንት፦ አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ፦ ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ። ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ፦ በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት አሉ። ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፥ በፊታቸውም ተጫወተ፥ ተዘባበቱበትም፥ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት። ሶምሶንም እጁን የያዘውን ብላቴና፦ ቤቱን የደገፉትን ምሰሶች እጠጋባቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ አስይዘኝ አለው። በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፥ የፍልስጥኤምም መኳንንት ሁሉ በዚያ ነበሩ፥ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። ሶምሶንም፦ ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፥ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ። ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶች ያዘ፥ አንዱን በቀኝ እጁ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ተጠጋባቸው። ሶምሶንም፦ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት አለ፥ ተጎንብሶም ምሰሶቹን በሙሉ ኃይሉ ገፋ፥ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፥ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ። ወንድሞቹም የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፥ ይዘውም አመጡት፥ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት። እርሱም በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።

መሳፍንት 16:4-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ወደደ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ወደ እርስዋ ሄደው እንዲህ አሉአት፤ “ሶምሶንን አግባብተሽ ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘው ከምን እንደ ሆነና እንዴትስ አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማድረግ ልናሸንፈው እንደምንችል ጠይቂው፤ እያንዳንዳችንም አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር እንሰጥሻለን።” ስለዚህ ደሊላ ሶምሶንን “ይህን ያኽል ብርቱ የሚያደርግህ ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ፤ አንድ ሰው አንተን አስሮ ሊያደክምህ የሚችለው እንዴት ነው?” አለችው። ሶምሶንም “እርጥብ በሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች እርጥብ የሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮችን ለደሊላ ይዘውላት መጡ፤ እርስዋም በእርሱ ሶምሶንን አሰረችው። በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ አሁንም ብርታት የሚያገኝበትን ምሥጢር ገና አልደረሱበትም ነበር። ደሊላም ሶምሶንን “እነሆ! አታለልከኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ!” አለችው። እርሱም “ሥራ ባልተሠራበት አዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” ሲል መለሰላት። ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ አሰረችው፤ በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ገመዱን ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። ደሊላም ሶምሶንን “እስከ አሁን ድረስ አሞኘኸኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ” አለችው። እርሱም “የራሴን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ብትጐነጒኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ ደሊላ ተኝቶ ሳለ የራሱን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒና በችካል ቸከለችው፤ ከዚያ በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች፤ እርሱ ግን ከእንቅልፉ ነቅቶ ጠጒሩን ከችካሉና ከድሩ ላይ ነቀለው። ስለዚህ እርስዋ “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት እወድሻለሁ ትለኛለህ? ሦስት ጊዜ አታለልከኝ፤ እስከ አሁንም ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘኸው ከምን እንደ ሆነ አልነገርከኝም” አለችው። ዕለት ዕለትም እየነዘነዘች ሞቱን እስከሚመኝ ድረስ አስጨነቀችው፤ በመጨረሻ እውነቱን ነገራት፤ እንዲህም አላት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆነ ጠጒሬ ተላጭቶ አያውቅም፤ ጠጒሬ ቢላጭ ግን ኀይል ተለይቶኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ።” ደሊላ እውነቱን እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ “እውነቱን ስለ ነገረኝ አንድ ጊዜ ተመልሳችሁ ኑ” ስትል ወደ ፍልስጥኤማውያን ገዢዎች መልእክት ላከች። እነርሱም ብሩን ይዘው መጡ። ደሊላ ሶምሶንን በጭንዋ ላይ አስተኝታ፤ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገች። አንድ ሰውም ጠርታ ሰባቱን የጠጒሩን ቁንዳላዎች እንዲቈረጡ አደረገች፤ ኀይሉም ከእርሱ ተለይቶት ስለ ነበር በማዋረድ ታስጨንቀው ነበር፤ ከዚያም በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው፤ እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ “እንደ ወትሮው በጣጥሼ እሄዳለሁ” ብሎ አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተለየው አላወቀም ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ከማረኩት በኋላ ሁለቱን ዐይኖቹን አወጡ፤ ወደ ጋዛም ወስደው በነሐስ ሰንሰለት በማሰር በታሰረበት ቤት እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤ የተቈረጠውም የራሱ ጠጒር እንደገና ማደግ ጀመረ። “በጠላታችን በሶምሶን ላይ ድልን እንድንቀዳጅ አድርጎናል” ብለው የደስታ በዓል ለማዘጋጀትና ለአምላካቸውም ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እርሱንም ባዩት ጊዜ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን ለእኛ አሳልፎ ሰጠን” እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ እንዲጫወትልን ሶምሶንን ጥሩት አሉ ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፤ በፊታቸውም ተጫወተ፤ በምሰሶና በምሰሶ መካከል አቆሙት። ሶምሶንም እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፥ “ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ምሰሶዎች አስጨብጠኝና እነርሱን ተደግፌ ልቁም” አለው። በሕንጻውም ውስጥ ብዙ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም የፍልስጥኤም ገዢዎች ሁሉ ነበሩ፤ በሰገነት ላይ ሆነው ሶምሶን ሲያጫውታቸው የሚመለከቱ ሦስት ሺህ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ሶምሶን “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ አስበኝ፤ አምላኬ ሆይ! እባክህ ኀይል ስጠኝና ፍልስጥኤማውያን ዐይኖቼን ስላወጡ አንድ ጊዜ ብቻ እንድበቀላቸው አድርገኝ!” ብሎ ጸለየ። ስለዚህ ሶምሶን ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ሁለቱን መካከለኛ ምሰሶዎች ጨበጠ፤ በቀኝ እጁ አንዱን ምሰሶ፥ በግራ እጁም ሌላውን ምሰሶ ይዞ ተጠጋ፤ “ሕይወቴ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ትለፍ!” ብሎ ጮኸ፤ በሙሉ ኀይሉም በገፋቸው ጊዜ ሕንጻው በፍልስጥኤም ገዢዎቹና እዚያ ባሉት ሁሉ ላይ ተደረመሰ፤ ሶምሶንም በሕይወቱ ሳለ ከገደላቸው ይልቅ በሞተበት ጊዜ የገደላቸው በዙ። ወንድሞቹና የቀሩት ቤተሰቡ ሁሉ መጥተው አስከሬኑን ወሰዱት፤ ወስደውም በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል በሚገኘው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት፤ ሶምሶን ኻያ ዓመት ሙሉ እስራኤልን መራ።

መሳፍንት 16:4-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከጊዜ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፥ “እርሱን አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብይው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት። ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፥ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቊጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሳምሶንም፥ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው። ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፥ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደሆነ ሊታወቅ አልቻለም። ደሊላም ሳምሶንን፥ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው። እርሱም፥ “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፥ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው። ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፥ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም መልሶ፥ “የራስ ጠጉሬን ሰባት ቈንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጉነሽ በችካል ብትቸክይው፥ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ቈንዳላዎቹን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤ ከችካልም ጋር ቸከለችው። እንደገናም፥ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፥ ከነቈንዳላው ነቀለው። ከዚያም፥ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኃይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው። በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው። ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንኩ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጉር ቢላጭ ግን ኃይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላ ሁሉንም ነገር እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ፥ ለፍልስጥኤማውያን ገዦች “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና ተመልሳችሁ ኑ” ብላ ላከችባቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም ብሩን ይዘው ተመልሰው መጡ። ደሊላ፥ ሳምሶንን በጭኗ ላይ አስተኝታ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገች በኋላ አንድ ሰው ጠርታ ሰባቱን የጠጉር ቈንዳላዎቹን አስላጨቻቸው፤ እርሷም ታስጨንቀው ጀመር፤ ኃይሉም ተለየው። እርሷም፥ “ሳምሶን፤ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቅቶ፥ “እንደ ወትሮው አደርጋለሁ” አለ፤ ነገር ግን ጌታ እንደ ተወው አላወቀም ነበር። ከዚያም ፍልስጥኤማውያን ያዙት፤ ዐይኖቹን አውጥተው ወደ ጋዛ ይዘውት ወረዱ፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም እስር ቤት ውስጥ እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤ ነገር ግን ከተላጨ በኋላ ጠጉሩ እንደገና ማደግ ጀመረ። በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፥ “አምላካችን ዳጎን፥ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ፥ አምላካቸውን ዳጎንን በማመስገን፥ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ብዙ ሰው የገደለብንን፥ ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ። እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፥ “እንዲያዝናናን ሳምሶንን አምጡት” አሉ፤ ስለዚህ ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠርተው አስመጡት፤ በፊታቸውም ተጫወተ። በምሶሶዎቹ መካከል ባቆሙት ጊዜ፥ ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፥ “ቤተ ጣዖቱ ደግፈው ወደ ያዙት ምሰሶዎች አስጠጋኝና ልደገፋቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ቤተ ጣዖቱን ሞልተውት ነበር፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም በሙሉ በዚያ ነበሩ፤ ሳምሶን ሲጫወት ለማየት ሦስት ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ። ሳምሶንም ወደ ጌታ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።” ከዚያም ቤተ ጣዖቱን መካከል ላይ ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አንዱን በቀኙ፥ አንዱን በግራ እጁ አቅፎ በመያዝ፥ “ከፍልስጥኤማውያን ጋር አብሬ ልሙት” በማለት ባለ ኃይሉ ሲገፋው፥ ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው፤ ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤተሰብ ሬሳውን ለማምጣት ወደዚያ ወረዱ፤ አምጥተውም የአባቱ የማኑሄ መቃብር ባለበት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ቀበሩት። ሳምሶን እስራኤልን ለሃያ ዓመት መሪ ሆኖ ነበር።