ከዚህ በኋላ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ወደደ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ወደ እርስዋ ሄደው እንዲህ አሉአት፤ “ሶምሶንን አግባብተሽ ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘው ከምን እንደ ሆነና እንዴትስ አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማድረግ ልናሸንፈው እንደምንችል ጠይቂው፤ እያንዳንዳችንም አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር እንሰጥሻለን።” ስለዚህ ደሊላ ሶምሶንን “ይህን ያኽል ብርቱ የሚያደርግህ ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ፤ አንድ ሰው አንተን አስሮ ሊያደክምህ የሚችለው እንዴት ነው?” አለችው። ሶምሶንም “እርጥብ በሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች እርጥብ የሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮችን ለደሊላ ይዘውላት መጡ፤ እርስዋም በእርሱ ሶምሶንን አሰረችው። በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ አሁንም ብርታት የሚያገኝበትን ምሥጢር ገና አልደረሱበትም ነበር። ደሊላም ሶምሶንን “እነሆ! አታለልከኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ!” አለችው። እርሱም “ሥራ ባልተሠራበት አዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” ሲል መለሰላት። ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ አሰረችው፤ በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ገመዱን ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። ደሊላም ሶምሶንን “እስከ አሁን ድረስ አሞኘኸኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ” አለችው። እርሱም “የራሴን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ብትጐነጒኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ከዚህ በኋላ ደሊላ ተኝቶ ሳለ የራሱን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒና በችካል ቸከለችው፤ ከዚያ በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች፤ እርሱ ግን ከእንቅልፉ ነቅቶ ጠጒሩን ከችካሉና ከድሩ ላይ ነቀለው። ስለዚህ እርስዋ “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት እወድሻለሁ ትለኛለህ? ሦስት ጊዜ አታለልከኝ፤ እስከ አሁንም ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘኸው ከምን እንደ ሆነ አልነገርከኝም” አለችው። ዕለት ዕለትም እየነዘነዘች ሞቱን እስከሚመኝ ድረስ አስጨነቀችው፤ በመጨረሻ እውነቱን ነገራት፤ እንዲህም አላት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆነ ጠጒሬ ተላጭቶ አያውቅም፤ ጠጒሬ ቢላጭ ግን ኀይል ተለይቶኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ።” ደሊላ እውነቱን እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ “እውነቱን ስለ ነገረኝ አንድ ጊዜ ተመልሳችሁ ኑ” ስትል ወደ ፍልስጥኤማውያን ገዢዎች መልእክት ላከች። እነርሱም ብሩን ይዘው መጡ። ደሊላ ሶምሶንን በጭንዋ ላይ አስተኝታ፤ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገች። አንድ ሰውም ጠርታ ሰባቱን የጠጒሩን ቁንዳላዎች እንዲቈረጡ አደረገች፤ ኀይሉም ከእርሱ ተለይቶት ስለ ነበር በማዋረድ ታስጨንቀው ነበር፤ ከዚያም በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው፤ እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ “እንደ ወትሮው በጣጥሼ እሄዳለሁ” ብሎ አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተለየው አላወቀም ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ከማረኩት በኋላ ሁለቱን ዐይኖቹን አወጡ፤ ወደ ጋዛም ወስደው በነሐስ ሰንሰለት በማሰር በታሰረበት ቤት እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤ የተቈረጠውም የራሱ ጠጒር እንደገና ማደግ ጀመረ። “በጠላታችን በሶምሶን ላይ ድልን እንድንቀዳጅ አድርጎናል” ብለው የደስታ በዓል ለማዘጋጀትና ለአምላካቸውም ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እርሱንም ባዩት ጊዜ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን ለእኛ አሳልፎ ሰጠን” እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ እንዲጫወትልን ሶምሶንን ጥሩት አሉ ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፤ በፊታቸውም ተጫወተ፤ በምሰሶና በምሰሶ መካከል አቆሙት። ሶምሶንም እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፥ “ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ምሰሶዎች አስጨብጠኝና እነርሱን ተደግፌ ልቁም” አለው። በሕንጻውም ውስጥ ብዙ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም የፍልስጥኤም ገዢዎች ሁሉ ነበሩ፤ በሰገነት ላይ ሆነው ሶምሶን ሲያጫውታቸው የሚመለከቱ ሦስት ሺህ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ሶምሶን “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ አስበኝ፤ አምላኬ ሆይ! እባክህ ኀይል ስጠኝና ፍልስጥኤማውያን ዐይኖቼን ስላወጡ አንድ ጊዜ ብቻ እንድበቀላቸው አድርገኝ!” ብሎ ጸለየ። ስለዚህ ሶምሶን ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ሁለቱን መካከለኛ ምሰሶዎች ጨበጠ፤ በቀኝ እጁ አንዱን ምሰሶ፥ በግራ እጁም ሌላውን ምሰሶ ይዞ ተጠጋ፤ “ሕይወቴ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ትለፍ!” ብሎ ጮኸ፤ በሙሉ ኀይሉም በገፋቸው ጊዜ ሕንጻው በፍልስጥኤም ገዢዎቹና እዚያ ባሉት ሁሉ ላይ ተደረመሰ፤ ሶምሶንም በሕይወቱ ሳለ ከገደላቸው ይልቅ በሞተበት ጊዜ የገደላቸው በዙ። ወንድሞቹና የቀሩት ቤተሰቡ ሁሉ መጥተው አስከሬኑን ወሰዱት፤ ወስደውም በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል በሚገኘው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት፤ ሶምሶን ኻያ ዓመት ሙሉ እስራኤልን መራ።
መጽሐፈ መሳፍንት 16 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 16:4-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos