የያዕቆብ መልእክት 5
5
ለባለጠጎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1አሁንም እናንተ ባለጠጎች! ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። 2ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። 3ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። 4እነሆ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፤ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቶአል። 5በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። 6ጻድቁን ኰንናችሁታል፤ ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም።
ስለ ትዕግሥትና ጸሎት
7እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። 8እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። 9ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። 10ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። 11እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፤ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።
12ከሁሉም በፊት ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይም ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፤ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን።
13ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። 14ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። 15የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። 16እርስ በርሳችሁ በኀጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች። 17ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፤ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ 18ሁለተኛም ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፤ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።
19ወንድሞች ሆይ! ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ 20ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኀጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።
Currently Selected:
የያዕቆብ መልእክት 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ