የያዕቆብ መልእክት 4
4
ዓለምን መውደድ
1በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በአካላችሁ ክፍሎች ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? 2ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ 3ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። 4አመንዝሮች ሆይ! ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5ወይስ መጽሐፍ “በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል፤” ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? 6ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል፤” ይላል። 7እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች! እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ! ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁና እዘኑ፤ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ሐዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፤ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።
በሰው ላይ መፍረድ እንደማይገባ
11ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል፤ በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ስለ ትምክሕት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
13አሁንም “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን፤ በዚያም ዓመት እንኖራለን፤ እንነግድማለን፤ እናተርፍማለን፤” የምትሉ እናንተ! ተመልከቱ፤ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። 14ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። 15በዚህ ፈንታ “ጌታ ቢፈቅድ፥ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን፤” ማለት ይገባችኋል። 16አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኀጢአት ነው።
Currently Selected:
የያዕቆብ መልእክት 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ