ትንቢተ ኢሳይያስ 66
66
እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድን ነው? 2ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፤ ይህም ሁሉ የእኔ ነው፥” ይላል እግዚአብሔር፤ “ወደ የዋሁና ወደ ጸጥተኛው፥ ከቃሌም የተነሣ ወደሚንቀጠቀጥ ሰው ከአልሆነ በቀር ወደ ማን እመለከታለሁ? 3በሬን የሚሠዋልኝ ኃጥእ ውሻን እንደሚያርድልኝ ነው፤#ዕብ. “በሬን የሚሠዋልኝ ሰውን እንድሚገድል ነው ጠቦትንም የሚሠዋ ...” የሚል ይጨምራል። የእህልን ቍርባን የሚያቀርብም የእሪያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንንም ለመታሰቢያ የሚያጥን አምላክን እንደሚፀርፍ ነው፤ እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል። 4እኔ ግን አዋርዳቸው ዘንድ፥ ስለ ኀጢአታቸውም እበቀላቸው ዘንድ እፈቅዳለሁ፤ እኔ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝም፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጉ፤ ያልወደድሁትንም መረጡ።”
5በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ “የእግዚአብሔር ስም ይከብር ዘንድ፦ ደስታችሁም ይገለጥ ዘንድ፥ እነርሱም ያፍሩ ዘንድ የሚጠሏችሁንና የሚጸየፉአችሁን ወንድሞቻችን በሏቸው። 6የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹም ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።
7“ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። 8ከቶ እንዲህ ያለ ነገርን ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገርን ማን አይቶአል? በውኑ ሀገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። 9እኔ ተስፋን ሰጠሁሽ፤ አንቺ ግን አላሰብሽኝም ይላል እግዚአብሔር። ሴት እንድትወልድ፥ መካንም እንዳትሆን የማደርግ እኔ አይደለሁምን?” ይላል አምላክሽ።
10ኢየሩሳሌም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እርስዋንም የምትወድዱአት ሁሉ፥ በአንድነት ሐሤት አድርጉ፤ ስለ እርስዋም ያለቀሳችሁ ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ 11ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናቷም ጡት ትጠግቡ ዘንድ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ።
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ልጆቻቸውንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በጕልበታቸውም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏቸዋል። 13እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። 14ታያላችሁ፤ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፤ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፤ ዐላውያንንም ያጠፋቸዋል።”
15እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ እንደ እሳት ይመጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። 16ምድርም ሁሉ በእግዚአብሔር እሳት ሰውም ሁሉ በሰይፉ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ተቀሥፈው የሞቱት ይበዛሉ። 17“በአትክልት ቦታ ውስጥ ሰውነታቸውን የሚያጠሩና የሚያነጹ፥ በምግብ ቦታም የእሪያን ሥጋ፥ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
18“ሥራቸውንና አሳባቸውን ዐውቄአለሁ፤ እነሆም እኔ እመጣለሁ፤ አሕዛብንና ልሳናትንም ሁሉ እሰበስባለሁ፤ እነርሱም ይመጣሉ፤ ክብሬንም ያያሉ። 19በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም ከሞት የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ኤላድ#“ኤላድ” ግሪክ ነው። በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬን ይናገራሉ። 20የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎዎች፥ በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 21ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
22“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 23እንዲህም ይሆናል፦ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በኢየሩሳሌም በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 24ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸውም አይጠፋም፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ ምሳሌ ይሆናሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 66: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ