ትንቢተ ኢሳይያስ 45
45
እግዚአብሔር ቂሮስን ለንጉሥነት እንደ መረጠ
1እግዚአብሔር አምላክ ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ኀይል እጥል ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ 2“በፊትህ እሄዳለሁ፤ ተራሮችንም ዝቅ አደርጋለሁ፤ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ፤ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ 3በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበሩትን መዛግብት እሰጥሃለሁ፤ የማይታየውንም የተደበቀውን ሀብት እገልጥልሃለሁ። 4ስለ አገልጋዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ ተቀበልሁህም፤ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 5እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አጸናሁህ፤ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 6በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም። 7ብርሃንን ፈጠርሁ፤ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ሰላምንም አደርጋለሁ፤ ክፋትንም አመጣለሁ፤ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
8“ሰማይ በላይ ደስ ይበለው፤ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም መድኀኒትን ታብቅል፤ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ፈጥሬሃለሁ።
9“እንደ ሸክላ ሠሪ ሥራ ውብ አድርጌ ሠራሁህ፤ ምድርን የሚያርስ ሁልጊዜ ያርሳልን? ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? እጅ የለህምና መሥራት አትችልም ይለዋልን? ጭቃ ሠሪውን ይከራከረዋልን? 10አባቱን፦ ለምን ወለድኸኝ? እናቱንም፦ ለምን አምጠሽ ወለድሽኝ? ለሚል ወዮ!
11“የእስራኤልም ቅዱስ የሚመጣውንም የፈጠረ#ዕብ. “የእስራኤል ቅዱስ፥ ሠሪውም፥ እንዲህ ይላል፦ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ ...” ይላል። እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጠይቁኝ፤ ስለ እጄም ሥራ እዘዙኝ። 12እኔ ምድርን ሠርቻለሁ፤ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን አጽንቼአለሁ፤ ከዋክብቶቻቸውንም#ዕብ. “ሰራዊታቸውንም” ይላል። ሁሉ አዝዣለሁ። 13እኔ ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ፤ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፤ በዋጋም ወይም በጉቦ ሳይሆን ምርኮኞችን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
14የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ግብፅና የኢትዮጵያ ንግዶች ደከሙ፤ ቁመተ ረዥሞች የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይገዙልሃል፤ እጆቻቸውን ታስረው በኋላህ ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፤ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። 15አንተ እግዚአብሔር ነህ፤ የእስራኤልም መድኀኒት አምላክ እንደ ሆንህ አላወቅንህም።#ዕብ. “የእስራኤል አምላክ መድኀኒት ሆይ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ” ይላል። 16የሚቃወሙት ሁሉም ያፍራሉ፤ ይዋረዱማል፤ አፍረውም ይሄዳሉ። 17ደሴቶች ሆይ፥ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘለዓለማዊ መድኀኒት ያድነዋል፤ እናንተም ለዘለዓለም አታፍሩምና አቷረዱም።”
18ሰማይን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። 19በስውር ወይም በጨለማ ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ ጽድቅን የምናገር፥ ቅን ነገርንም የምናገር እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 20እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ፤ በአንድነትም ተማከሩ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ ዕውቀት የላቸውም። 21የሚናገሩ ከሆነ ከጥንት ጀምሮ ይህን ምስክርነት ያደረገ ማን እንደ ሆነ በአንድነት ያውቁ ዘንድ ይቅረቡ። ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኀኒት ነኝ፥ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 22እናንተ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ተመለሱ፤ ትድኑማላችሁ። 23ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፤ አትመለስምም፤ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ በእግዚአብሔር ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።” 24ክብርና ጽድቅ ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ከእግዚአብሔርም የሚርቁ ሁሉ ያፍራሉ። 25የእስራኤልም ልጆች ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ይከብራሉም ይባላል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 45: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ