ትንቢተ ኢሳይያስ 43
43
1አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዝአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ተቤዥችሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ። 2በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ወንዞችም አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። 3እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኀኒትህ ነኝ፤ ግብፅንና ኢትዮጵያን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ሴዎንንም#ዕብ. “ሳባን” ይላል። ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። 4በፊቴ የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ብዙ ሰዎችን ለአንተ ቤዛ፥ አለቆችንም ለራስህ እሰጣለሁ። 5እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፤ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። 6ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፤ ደቡብምን፦ አትከልክል፤ ወንዶች ልጆችን ከሩቅ፥ ሴቶች ልጆችንም ከምድር ዳርቻ፥ 7በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” እለዋለሁ።
8ዐይኖች እያሉአቸው የማያዩ ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም እያሉአቸው የማይሰሙ ደንቆሮዎችን አወጣሁ። 9አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ አለቆችም ተከማቹ፤ ይህን ማን ይናገራል? የቀድሞውንስ ማን ይነግራችኋል? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፤ ሰምተውም፦ እውነትን ይናገሩ። 10ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ፥ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮች ሁኑ፤ እኔም ምስክር እሆናችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር አምላክ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልነበረም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። 11እኔ፥ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ የሚያድን አምላክ የለም። 12ተናግሬአለሁ፤ አድኜማለሁ፤ መክሬማለሁ፤ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምልኮ አልነበረም፤ ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮች ናችሁ፤ 13ከጥንት ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፤ ወደ ኋላስ የሚመልስ ማን ነው?
14የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፤ ስደተኞችን አስነሣለሁ፤ ከለዳውያንም በመርከብ ውስጥ ይታሰራሉ። 15ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር አምላክ እኔ ነኝ።” 16በባሕር ውስጥ መንገድን በኀይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደረገ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ 17እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፤ አይነሡም፤ ቀርተዋል፤ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ 18የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፤ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። 19እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፤ እናንተም አታውቁትም፤ በምድረ በዳም መንገድን፥ በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። 20የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል። የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን፥ በበረሃም ወንዞችን ሰጥቻለሁና፤ 21እነርሱም ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርኋቸው ሕዝብ ናቸው፤
22ያዕቆብ ሆይ፥ እነሆ፥ አልጠራሁህም፤ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አልዘበዘብሁህም፤ 23ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም፤ በሌላም በሚቃጠል መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም፤ በዕጣንም አላደከምሁህም። 24ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም፤ የመሥዋዕትህንም ስብ አልተመኘሁም፤ ነገር ግን በኀጢአትህና በበደልህ በፊቴ ቁመሃል።
25መተላለፍን፦ ስለ እኔ ስለ ራሴ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኀጢአትህንም አላስብም። 26አሳስበኝ፤ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ አስቀድመህ በደልህን ተናገር። 27በመጀመሪያ አባቶችህ፥ ቀጥሎም አለቆችህ በድለውኛል። 28አለቆች መቅደሴን አረከሱ፤ ስለዚህም ያዕቆብን ለጥፋት፥ እስራኤልንም ለውርደት ሰጠሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 43: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ