ትንቢተ ኢሳይያስ 40
40
ለእስራኤል ሕዝብ የተነገረ ተስፋ
1አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ 2ካህናት ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ወደ ልቧ የሚገባ ነገርን ተናገሩ፤ ውርደቷ እንደ ተፈጸመ፥ ኀጢአቷም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኀጢአቷ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች አጽናኑአት።
3የዐዋጅ ነጋሪ ቃል በምድረ በዳ፥ “የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሃ አስተካክሉ። 4ሸለቆው ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም ይቅና፤ ሰርጓጕጡም ሜዳ ይሁን፤ 5የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትድግና ይይ፤ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።”
6“ጩኽ” የሚል ሰው ቃል፤ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ። “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፤ የሰውም ክብሩ ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነው። 7የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። 8ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”
9ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለኢየሩሳሌም የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ድምፅህን በኀይል አንሣ፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለህ ንገር። 10እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር በኀይሉ ይመጣል፤ በክንዱም ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው። 11መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፤ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።
12ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝሩ የለካ፥ ምድርንም ሁሉ ሰብስቦ በእጁ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን፥ ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? 13የእግዚአብሔርን ሕሊና ያወቀ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያማከረው ማን ነው? 14ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? ፍርድንስ ማን አስተማረው? የጥበብንስ መንገድ ማን አሳየው? 15እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤ እንደ ሚዛንም ውልብልቢት ተቈጥረዋል፤ እንደ ኢምንትም ናቸው። 16ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። 17አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ እንደ ከንቱ ነገርም ይመስላሉ።
18እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? 19እንጨት ጠራቢ በሠራው ምስል፥ ወይስ አንጥረኛ መትቶ በሠራው ወርቅ፥ በወርቅም ለብጦ በሠራው ምስል ትመስሉታላችሁን? 20ጠራቢው የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። 21አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? 22እርሱ የምድርን ክበብ ያጸናል፤ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው፥ እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚዘረጋቸው፤ 23አለቆችንም የሚገዛላቸው እንዳይኖር የሚያደርግ ምድርንም እንደ ኢምንት የሚያደርጋት እርሱ ነው። 24በእርሱም ላይ ዛፉንና ሣሩን፥ የማይቈጠር ሌላውንም ብዙ ፍጥረት የፈጠረ እርሱ ነው። ነፋስም በነፈሰባቸው ጊዜ ይደርቃሉ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ይጠርጋቸዋል።
25እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር። 26ዐይናችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ ይህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? ከዋክብትንም በሙሉ የሚቈጥራቸው እርሱ ነው፤ በየጊዜያቸው ያመጣቸዋል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በክብሩ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።
27ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፥ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ አምላኬም ከእኔ ርቋል፤ ፍርዴንም ትትዋል፤ ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? 28አሁንም አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘለዓለም አምላክ፥ የምድርንም ዳርቻ የፈጠረ አምላክ ነው፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። 29ለደካሞች#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለተራቡት” ይላል። ኀይልን ይሰጣል፤ መከራ የሚቀበሉትንም አያሳዝናቸውም። 30ብላቴኖች ይራባሉ፤ ጐልማሶች ይታክታሉ፤ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይዝላሉ። 31እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉና የሚታገሡ ግን ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር ክንፍ ያወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱምም፤ ይሄዳሉ፤ አይራቡምም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 40: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ