ትንቢተ ኢሳይያስ 41
41
ለእስራኤል የተሰጠ ዋስትና
1ደሴቶች ሆይ፥ ወደ እኔ ተመለሱ፤ አለቆች ኀይላቸውን ያድሳሉና በአንድነት ቀርበው ፍርድን ይናገሩ። 2ከምሥራቅ ጽድቅን ያስነሣ፥ ይከተለውም ዘንድ ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? በአሕዛብና በነገሥታት ፊት ድንጋጤን ያመጣል። ጦሮቻቸውን በምድር ያስጥላቸዋል፤ ቀስቶቻቸውም እንደ ገለባ ይረግፋሉ። 3ያሳድዳቸዋልም፤ እግሮቹም በሰላም መንገድ ይሄዳሉ። 4ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ፊተኛውና ኋለኛው እኔ ነኝ።
5አሕዛብ አይተው ፈሩ። የምድርም ዳርቾች ቀረቡ፤ በአንድነትም ቀረቡ፤ መጡም። 6ሁሉም ባልንጀራውን ይከራከራል፤ ሁሉም እያንዳንዱ ወንድሙ ይረዳው ነበር፤ ወንድሙንም፦ አይዞህ ይለው ነበር። 7አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፤ ስለ ማጣበቅ ሥራውም፥ “መልካም ነው” አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው።
8ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ 9አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ፥ ከማዕዘንዋም የጠራሁህ ነህና፦ አንተ ባሪያዬ ነህ፤ መርጬሃለሁ፤ አልጥልህም፤ ያልሁህ ሆይ፥ 10እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። 11እነሆ፥ የሚቃወሙህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዱማል፤ እንዳልነበሩም ይሆናሉ፤ ጠላቶችህም ይጠፋሉ። 12የሚያሠቃዩህንም ሰዎች ትሻቸዋለህ፤ አታገኛቸውምም፤ እንዳልነበሩ ይሆናሉና፤ የሚዋጋህም የለም። 13ቀኝ እጅህን የያዝሁህ፥ እንዲህም የምልህ እኔ አምላክህ ነኝና። 14#ዕብ. “ትል ያዕቆብ ሆይ” ይላል።ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቍጥር ጥቂት የነበርህ እስራኤል ሆይ፥ እኔ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። 15እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ፤ ኮረብቶችንም ታደቅቃቸዋለህ እንደ ገለባም ታደርጋቸዋለህ። 16ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእስራኤል ቅዱስ ደስ ይልሃል።
17ድሆችና ምስኪኖች ውኃ ይሻሉ፤ አያገኙምም፤ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፤ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። 18በተራሮች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የተጠማችውንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። 19በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን፥ ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፤ 20ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ይህን ሁሉ እንደ ሠራ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ይህን እንደ አሳየ ያውቁ ዘንድ፥ ያስተውሉም ዘንድ፥ ይረዱም ዘንድ፥ ያምኑም ዘንድ ነው።
21ፍርዳችሁ ቀረበች፥ ይላል እግዚአብሔር አምላክ፤ ምክራችሁም ቀረበ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። 22ይምጡ፤ የሚደርስባችሁንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ፤ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ንገሩን፤ የሚመጡትንም አሳዩን። 23አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እናደንቃችሁም ዘንድ፥ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ። 24እናንተ ከየት ናችሁ? ከየትስ ሠሯችሁ? ከምድር የሚመርጧችሁም የረከሱ አይደሉምን?
25ከሰሜንና ከፀሐይ መውጫ የሚመጡትን አስነሣሁ፤ በስሜም ይጠራሉ፤ አለቆች ይምጡ፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃና ጭቃን እንደሚረግጥ ሸክላ ሠሪ እንዲሁ ይረግጡአቸዋል። 26እናውቅ ዘንድ፥ ከጥንት የተነገረው፦ እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? ከመሆኑ በፊት የሚናገር የለም፤ የሚገልጥም የለም፤ ቃላችሁን የሚሰማ የለም። 27በመጀመሪያ ለጽዮን፦ ግዛትን እሰጣታለሁ፤ ኢየሩሳሌምንም ወደ መንገድዋ እመልሳታለሁ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አጽናናታለሁ” ይላል። 28ከአሕዛብና ከአማልክቶቻቸው የሚናገር የለምና፥ ከየትም እንደ ሆኑ ብጠይቃቸው አይመልሱልኝም። 29የሚሠሩአቸውም በከንቱ ይሠሩአቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 41: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ