ትንቢተ ኢሳይያስ 36
36
ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ እንደ ዛተ
1እንዲህም ሆነ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በዐሥራ አራተኛው ዓመተ መንግሥት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው። 2የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው፤ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛዪቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ። 3የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሓፊውም ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።
4ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በማን ትተማመናለህ? 5በምክርና በከንፈር ንግግር ጦርነት ይሆናልን? አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 6እነሆ፥ በዚያ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 7አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትል፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሥዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን?#ግሪክ ሰባ. ሊ. ከዚህ ይለያል። 8አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተስማማ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶችን እሰጥሃለሁ። 9ከታናናሾቹ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን ጭፍራ ፊት መመለስ እንዴት ትችላለህ? ስለ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በግብፅ የሚታመኑ ለጌታዬ ባሮች ናቸው። 10አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ እናጠፋችሁ ዘንድ ወደዚህ ሀገር ዘምተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደ ሀገራቸው ዘምታችሁ አጥፉአቸው” አለን።
11ኤልያቄምና ሳምናስ፥ ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። 12ራፋስቂስ ግን፥ “ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፥ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ለተቀመጡት ሰዎች እነግራቸው ዘንድ አይደለምን?” አላቸው።
13ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። 14ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ በማይችል ቃል ሕዝቅያስ አያታልላችሁ። 15ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድናችኋል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም አይበላችሁ። 16ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በሕይወት ልትኖሩ ብትወድዱ ሁላችሁ ወደ እኔ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ትጠጣላችሁ፤ 17ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። 18ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ አያታልላችሁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት ሀገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 19የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 20እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ ሀገሮች አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ አለን?”
21እነርሱም ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 22የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፥ የሠራዊቱ ጸሓፊ ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 36: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ