ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት ሀገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብም ትውልድ እንዲህ ነው። ዮሴፍ ዐሥራ ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው ወደ እስራኤል ያመጣ ነበር። ያዕቆብም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወድደው ነበር፤ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና። በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወድደው በአዩ ጊዜ ጠሉት፤ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ፤ ለወንድሞቹም ነገራቸው። እርሱም አላቸው፥ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ፥ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆ፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች በዙርያ ከብበው እነሆ፥ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፥ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆነን ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አየ፤ ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ሕልሙም እንዲህ ነው፦ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ይሰግዱልኝ ነበር።” አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በውኑ እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር። ወንድሞቹም በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና” አለው። እርሱም፥ “እሺ” አለው። እርሱም፥ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። ወደ ኬብሮንም ቆላ ላከው፤ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም፥ በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውየውም፥ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “ወንድሞችን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ?” አለ። ሰውየውም፥ “ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፤ በዶታይንም አገኛቸው።
ኦሪት ዘፍጥረት 37 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 37:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች