ዘፍጥረት 37:1-17

ዘፍጥረት 37:1-17 NASV

ያዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋራ የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለ ወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ። እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለ ወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወድደው ነበር፤ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብም አደረገለት። ወንድሞቹም፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወድደው መሆኑን ሲያዩ፣ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልም ዐለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ ስሙኝ እኛ ሁላችን በዕርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ በድንገት ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች ዙሪያዋን ከብበው ለእኔ ነዶ ሰገዱላት።” ወንድሞቹም፣ “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት፤ ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት። እንደ ገናም ሌላ ሕልም ዐለመ፤ ለወንድሞቹም፣ “እነሆ፤ ሌላ ሕልም ዐለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው። ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ “ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው። ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው። ከዚህም በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ወደ ሴኬም አካባቢ ሄዱ፤ እስራኤልም ዮሴፍን “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ።” አለው። ዮሴፍም “ይሁን ዕሺ” አለው። ያዕቆብም፣ “ሄደህ ወንድሞችህም፣ መንጎቹም ደኅና መሆናቸውን አይተህ ወሬያቸውን አምጣልኝ” አለው፤ ከኬብሮንም ሸለቆ ወደ ሴኬም ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣ ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው። ሰውየውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም፣ ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ ዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}