ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ የሚያደርገውንም አጣ። ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች ላሞችንም፥ ግመሎችንም፥ በጎችንም ሁለት ወገን አድርጎ ከፈላቸው፤ ያዕቆብም እንዲህ አለ፥ “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ይድናል።” ያዕቆብም አለ፥ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፤ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለባሪያህ በአደረግኸው በምሕረትህና በእውነትህም ሁሉ በጎውን አድርግልኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። አቤቱ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናትን ከልጆችዋ ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። አንተም፦ ‘በርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።’ ” በዚያችም ሌሊት በዚያው አደረ። ለወንድሙ ለዔሳውም የሚወስደውን እጅ መንሻ አወጣ፤ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሃያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሃያ የበግ አውራዎችን፥ ሃምሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሃያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም የአህያ ውርንጫዎች፤ መንጎቹንም ለየብቻ ከፍሎ ለብላቴኖቹ ሰጣቸው፤ ብላቴኖቹንም፥ “በፊቴ እለፉ፤ መንጋውን ከመንጋው አርቁ” አላቸው። የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደ ሆነ፦ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለሀ? በፊትህ ያለው ይህስ መንጋ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ በዚያ ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የአገልጋይህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ተከትሎናል’ በለው።” እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን፥ በፊቱ የሚሄዱትንና መንጋውን የሚነዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ፦“ ወንድሜ ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤ እንዲህም በሉ፦ እነሆ አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል፤ ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።” እጅ መንሻውን ከእርሱ አስቀድሞ ላከ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።
ኦሪት ዘፍጥረት 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 32:7-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች