ከዚህም በኋላ አብራም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው “በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ።” አብራምም በግንባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም አብራምን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ቃል ኪዳኔን በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም ‘አብርሃም’ ይባላል እንጂ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም በጣም አበዛሃለሁ፤ ሕዝብም፥ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወጡ አደርግሃለሁ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል በትውልዳቸው ለዘለዓለም ኪዳን አቆማለሁ፤ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በውስጥዋ የምትኖርባትን ይህችን ምድር፥ የከነዓንን ምድር ሁሉ፥ ለዘለዓለም ይገዙአት ዘንድ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተ፥ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የሰውነታችሁን ቍልፈት ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ፥ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። በቤትህም የተወለደ፥ በብርም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆናል። በስምንተኛው ቀን የሥጋውን ቍልፈት ያልተገረዘ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።”
ኦሪት ዘፍጥረት 17 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች