ትንቢተ ሕዝቅኤል 6
6
እግዚአብሔር አምልኮ ጣዖትን እንደ ከለከለ
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና፤ ትንቢትም ተናገርባቸው። 3ለእስራኤል ተራሮች የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለምንጮችና ለሸለቆዎች እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ። 4መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ የፀሐይ ምስሎቻችሁም ይሰበራሉ፤ የተገደሉ ሰዎቻችሁንም በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች#“የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፤ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6በምትኖሩባትም ስፍራ ሁሉ ከተሞች ይፈርሳሉ፥ የኮረብታ መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፤ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ ባድማም ይሆናሉ፤ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ፤ ያልቃሉም፤ የፀሐይ ምስሎቻችሁም ይጠፋሉ፤ ሥራችሁም ይሻራል። 7ሙታኖቻችሁም በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
8“ነገር ግን በሀገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከእናንተ ከአሕዛብ ጦር የዳኑትን አስቀራለሁ። 9በዚያ በተማረኩበት በአሕዛብ ዘንድ ከእናንተ የዳኑት ያስቡኛል፤ ለሰሰኑበት፥ ከእኔም ለራቁበት ለልቡናቸው፥ ለሰሰኑ፥ ጣዖትንም ለተከተሉ ለዓይኖቻቸው ማልሁ፤ ጣዖቶቻቸውን ሁሉ እንዳመለኩ መጠን ስለ ሥራቸው ክፋት ፊታቸውን ይነጫሉ። 10እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ #ተከታዩ ዐረፍተ ነገር በግሪኩ የለም።ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ ለከንቱ አይደለም። 11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእጅህ አጨብጭብ፤ በእግርህም አሸብሽብ፤ ስለ እስራኤል ቤት ርኵሰት ሁሉ ወዮ ወዮ በል፤ በረኀብና በጦር፥ በቸነፈርም ይጠፋሉ። 12በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ በሀገር የቀረውና የተከበበውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ። 13ሬሳዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ በወደቁ ጊዜ በረዣዥም ኮረብታ ሁሉ፥ በተራሮችም ራሶች ሁሉ፥ በዕንጨቱም ጥላ ሥር ለጣዖቶቻቸው ሁሉ፥ መልካም መዓዛን ባጠኑበት ከቅጠሉ ሁሉ በታች ሬሳዎቻቸው በወደቁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 14እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፤#ግእዝ “ወእትነሣእ ላዕሌሆሙ” ይላል። በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ