ትንቢተ ሕዝቅኤል 7
7
የእስራኤል ፍጻሜ መቃረብ
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ፍጻሜ በእስራኤል ምድር ላይ መጣ፤ በምድሪቱ በአራቱም ማዕዘን ፍጻሜ መጣ። 3አሁንም ፍጻሜ በአንቺ ላይ ደርሶአል። ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፤ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 4ዐይኔም አይራራልሽም፤ እኔም ይቅር አልልሽም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”#ምዕ. 7 ቍ. 4 በግሪክ ሰባ. ሊ. ቍ. 6 ነው።
5ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ክፋት በክፋት ላይ፤ እነሆ ይመጣል። 6ፍጻሜ መጥቶአል፤ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ነቅቶብሻል፤ እነሆ ደርሶአል። 7በሀገር የምትኖር ሆይ! ስብራትህ ጊዜው ደረሰ፤ ቀኑም ቀረበ፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ የተራራ ላይ ዕልልታ አይደለም፤#ምዕ. 7 ቍ. 7 በግሪክ ሰባ. ሊ. ቍ. 4 ነው። 8አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፤ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፤ እንደመንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።#ምዕ. 7 ቍ. 8 በግሪክ ሰባ. ሊ. ቍ. 7 ነው። 9ዐይኔም አይራራም፤ እኔም ይቅር አልልም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10“እነሆ ቀኑ ደርሶአል፤ እነሆ! የእግዚአብሔር ቀን ወጥታለች፤ ስብራትህ ደርሶአል፤ ብትርም አብባለች፤ ስድብም በዝቶአል። 11የኀጢአተኛው ምርኩዝ ተሰበረ፤ በደል በዛች፤ ይኸውም በሁከት አይደለም፤ በችኮላም አይደለም።#ዕብ. “ግፍ ወደ ክፋት በትር ተነሥቶአል ፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው፥ ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም ፤ የሚያለቅስላቸውም የለም” ይላል። 12ጊዜው መጥቶአል፤ ቀኑ እነሆ ቀርቦአል፤ መቅሠፍቷ በሁለንተናዋ መልቶአልና#“መቅሠፍቷ በሁለንተናዋ ሞልቶአልና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የሚገዛ ደስ አይበለው፤ የሚሸጥም አይዘን። 13የገዛው ወደ ሻጩ አይመለስም፤ ዳግመኛም በሕይወት ይኖራል፤ ሁለንተናዋን አይቶአልና አልተመለሰም፤ የሰው ሕይወቱ በዐይኑ ፊት ነው።#ምዕ. 7 ቍ. 13 በግእዝ ብቻ ዕብ. “ሻጩ ወደ ሸጠው አይመለስም” ይላል።
14“መለከቱን ንፉ፤ ሁሉንም አዘጋጁ፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም። 15ሰይፍ በውጭ፥ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፤ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል። 16ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ፤ መብረርን እንደሚማር ርግብም#“መብረርን እንደሚማር ርግብም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በተራራ ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኀጢአታቸው ሁሉ እገድላለሁ። 17እጅ ሁሉ ትደክማለች፤ ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ይሆናል። 18ማቅም ትታጠቃላችሁ፤ ድንጋጤም ይሸፍናችኋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ ሐፍረት ይሆናል፤ በራሳችሁም ሁሉ ላይ ቡሃነት ይሆናል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. በሦስተኛ መደብ ይጽፋል። 19ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም ይረክሳል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው አያድናቸውም።#“በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው አያድናቸውም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እርሱ የኀጢአታቸው እንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉም። 20የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፤ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ። 21በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኀጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአቸዋል። 22ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ሥርዐቴንም ያረክሳሉ፤ ኀይለኞች ይገቡባታል፤ ያረክሱአትማል።
23“ምድር በአሕዛብ እንደ ተመላች፥ ከተማም በኀጢአት ተመልታለችና ሰንሰለት ሥራ።#“ሰንሰለት ሥራ” የሚለው በግእዝ የለም። 24ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ፤ ቤታቸውንም ይወርሳሉ፥#ምዕ. 7 ቍ. 24 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የኀያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። 25ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ፤ እርሱም አይገኝም። 26ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፤ ወዮታ በወዮታ ላይ ይከተላል፤ ከነቢዩም ዘንድ ራእይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ሕግ፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል። 27ንጉሡም ያለቅሳል፥#“ንጉሡም ያለቅሳል” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አለቃም ውርደትን ይለብሳል፤ የምድርም ሕዝብ እጅ ትሰላለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፤ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ