ትንቢተ ሕዝቅኤል 16
16
እምነት የጐደላት ኢየሩሳሌም
1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ለኢየሩሳሌም ኀጢአትዋን አስታውቃት፤ እንዲህም በላት፦ 3ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል፦ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ፤ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። 4በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልታተበም፤ ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ#“ንጹሕም ትሆኜ ዘንድ” የሚለው በዕብ. ብቻ። በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም። 5በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ፥ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዐይኔ አልራራልሽም፤ ማንም አላዘነልሽም።
6“በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ፤ በደምሽም ተለውሰሽ በአየሁሽ ጊዜ፦ ከደምሽ ዳኝ አልሁሽ፤ 7በእርሻ ላይ እንደ አለ ቡቃያ አበዛሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ታላቅም ሆንሽ፤ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ገባሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ፤ ጠጕርሽም አደገ፤ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፤ ተራቍተሽም ነበርሽ። 8በአንቺ ዘንድ በአለፍሁና በአየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ ጊዜሽ እንደ ደረሰ፥ በአንቺም የሚያድሩ ሰዎች ጊዜ እንደ ደረሰ አየሁ። እጆችን#ዕብ. “መጐናጸፊያዬን” ሲል ግሪክ ሰባ. ሊ. “ክንፎችን” ይላል። በላይሽ ዘረጋሁ፤ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም፤ ከአንቺም ጋራ ቃል ኪዳን ገባሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። 9በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ። 10ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ፤ ጥቁር#ዕብ. “በአቆስጣ ቁርበት” ይላል። ጫማም አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ፤ በሐርም ከደንሁሽ። 11በጌጥም አስጌጥሁሽ፤ በእጅሽም ላይ አንባር፥ በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ። 12በአፍንጫሽም ቀለበት፥#“በአፍንጫሽም ቀለበት” የሚለው በግእዝ የለም። በጆሮሽም ጉትቻ፥ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ። 13በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር፥ ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን፥ ዘይትንም በላሽ፤ ወፈርሽ፤ እጅግም ውብ ሆንሽ፤ ለመንግሥትም የተዘጋጀሽ አደረግሁሽ።#“ለመንግሥትም የተዘጋጀሽ አደረግሁሽ” የሚለው በግሪኩ የለም። 14ባንቺ ላይ ከአኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ስምሽ በአሕዛብ መካከል ተሰማ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15“ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል፤ በስምሽም አመንዝረሻል፤ ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። 16ከልብስሽም ወስደሽ በመርፌ የተጠለፉ ጣዖታትን ሠራሽ፤ አመነዘርሽባቸውም፤ ስለዚህ ፈጽመሽ አልገባሽም፤ ከእንግዲህም ወዲህ እንዲህ ያለ ነገር አይሆንም።#ዕብ. “ በኮረብቶች ላይ በዥንጉርጉር ልብስሽ ያስጌጥሻቸውን መስገጃዎች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም ፤ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም” ይላል። 17ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎችን ለራስሽ አድርገሻል፤ አመንዝረሽባቸውማል። 18ወርቀ ዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፤ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ። 19የሰጠሁሽንም እንጀራዬን፥ ያበላሁሽንም ዱቄትና ዘይቱን፥ ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፤ እንዲህም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው፤ ገደልሻቸውም። 21ልጆችን አረድሽ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን? 22ከኀጢአትሽና ከዝሙትሽ ሁሉ ይህ ይከፋል፤ አንቺ ዕራቁትሽን ሳለሽ፥ ኀፍረትም ሞልቶብሽ ሳለሽ፥ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ፥ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
23“ከዚህም ከክፋትሽ ሁሉ በኋላ ወዮልሽ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 24የምትሰስኝበትን ቤት ለራስሽ ሠራሽ፤ በአደባባዩ ሁሉ ከፍ ያለ ቦታን አደረግሽ። 25በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፤ ውበትሽንም አረከስሽ፤ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ፤ ዝሙትሽንም አበዛሽ። 26አካላቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብፃውያን ልጆች ጋር አመነዘርሽ፤ እኔንም ታስቆጭ ዘንድ ዝሙትሽን አበዛሽ። 27ስለዚህ እነሆ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ፤ ድርሻሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም፥ ከመንገድሽ ለመለሱሽና ለአሳቱሽ#ዕብ. “ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ” ይላል። ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። 28ከአሦራውያን ልጆች ጋር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከአሦራውያን ሴቶች ልጆች ጋር” ይላል። ፈጽመሽ አመነዘርሽ፤ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም፤ ዝሙትሽም አልበቃሽም። 29እስከ ከነዓን ምድር እስከ ከላውዴዎንም ድረስ ዝሙትሽን አበዛሽ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከከለዳውያን ጋር ቃል ኪዳንን አበዛሽ” ይላል። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
30“ይህን ሁሉ የሴሰኛ ሴት ሥራን ሠርተሻልና፥ ከሴቶች ልጆችሽም ጋር ሦስት ጊዜ አመንዝረሻልና ሴቶች ልጆችሽን ምን አደርጋቸዋለሁ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።#ዕብ. “የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ይላል። 31በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል፤ በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትሰበስብ እንደ ጋለሞታም አልሆንሽም። 32ከባልዋ ገንዘብ ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ። 33ለአመንዝራዎች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፤ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃን ትሰጫቸዋለሽ። 34ዝሙትሽ ከሌሎች ሴቶች ዝሙት ልዩ ነው፤ ማንም ለዝሙት የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል።
የእግዚአብሔር ፍርድ በኢየሩሳሌም ላይ
35“ስለዚህ ዘማ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። 36ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወርቄን በትነሻልና ከኀጢአት ምኞት በሠራሽው ዝሙት#ዕብ. “በርኵሳን ጣዖቶችሽ ሁሉ አምልኮት”ይላል። ኀፍረተ ሥጋሽን ገልጠሻልና በሰጠሻቸውም በልጆችሽ ደም፥ 37ስለዚህ እነሆ እኔ ከአንቺ ጋር አንድ የሆኑ ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤ የምትወጃቸውንም ከምትጠያቸው ጋር በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤ ይከቡሻል፤ በእነርሱም ዘንድ ጕስቍልናሽን እገልጥብሻለሁ፤ ሁሉም ኀፍረትሽን ያዩብሻል። 38በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች#“ደም አፍሳሾች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በቀል እበቀልሻለሁ፤ በመዓትና በቅንአት ደምም አስቀምጥሻለሁ። 39በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ፤ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል፤ የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፤ ዕራቁትሽንም ይተዉሻል፤ ቷረጃለሽም። 40ብዙ ሕዝብን ይሰበሰቡብሻል፤ በድንጋይም ይወግሩሻል፤ በሰይፋቸውም ይወጉሻል። 41ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ በብዙም ሴቶች ፊት ይበቀሉሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዋጋ አትሰጪም። 42መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ፤ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ደግሞም አልቈጣም። 43የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና፤ ስለዚህ እነሆ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እንደዚህም በበደልሽ ሁሉ ላይ ኀጢአትን ሠራሽ።#ዕብ. “ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም” ይላል።
ልጅቱ እንደ እናቷ
44“እነሆ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፥ እንደ እናቲቱ እንዲሁ ልጅቱ ናት፤ እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። 45አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላች የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች፤ አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። 46ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሽቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በሰተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። 47አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም፤ እንደ ኀጢአታቸውም አላደረግሽም፤ ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ኀጢአት አደረግሽ። 48እኔ ሕያው ነኝ! አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 49እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት፥ እንጀራን መጥገብ፥ መዝለልና ሥራን መፍታት፥ ይህ ሁሉ በእርስዋና በልጆችዋ ነበር፤ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። 50ኰርተው ነበር፤ በፊቴም ርኵስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ እንደ አየሁ አስወገድኋቸው። 51ሰማርያም የኀጢአትሽን እኩሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ኀጢአትን አበዛሽ፤ በሠራሽውም ኀጢአት ሁሉ አጸደቅሻቸው። 52አሁንም ከእነርሱ ይልቅ አብዝተሽ በሠራሽው ኀጢአትሽ እኅቶችሽን ስላረከስሻቸው ቅጣትሽን ተሸከሚ። ከአንቺም ይልቅ አጸደቅሻቸው፤ አንችም እፈሪ፤ እፍረትሽንም ተሸከሚ፤ እኅቶችሽን አጽድቀሻቸዋልና። 53ምርኮአቸውንም እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ እመልሳለሁ፤ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ። 54ፍዳሽንም ትቀበዪ ዘንድ በአስቈጣሽኝ ሥራሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ። 55እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፤ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። 56እኅትሽ ሰዶምም በትዕቢትሽ ቀን በአፍሽ አልተወሳችም። 57ክፋትሽ እንደ ዛሬው ሳይገለጥ ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጐረቤቶችዋ ሁሉ በዙሪያሽም ለሚከቡሽ ፍልስጥኤማውያት ሴቶች ልጆች መሰደቢያ ሆነሻል። 58ኀጢአትሽንና በደልሽን#ዕብ. “ዝሙትሽንና ርኵሰትሽን” ይላል። ተሽክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።
የዘለዓለም ቃል ኪዳን
59“ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ!#“መሐላን የናቅሽ ሆይ” የሚለው በዕብ. ብቻ። አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። 60ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ። 61ታላቆቹንና ታናሾቹን እኅቶችሽንም በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ፤ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፤ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም። 62እኔም ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 63ታስቢ ዘንድ፥ ታፍሪም ዘንድ፥ ደግሞም ስላደረግሽው ነገር ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ስለ ኀፍረትሽ አፍሽን ትከፍቺ ዘንድ አይቻልሽም፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 16: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ