ትንቢተ ሕዝቅኤል 17
17
ምዕራፍ 17።
የንስርና የወይን ተክል ምሳሌ
1የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ምሳሌ መስለህ ንገር፤ እንዲህም በል፦ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ታላቅ ክንፍ፥ ረጅምም ጽፍር ያለው፥ ላባንም የተሞላ፥ መልከ ዝንጉርጉር የሆነ#“ላባንም የተሞላ መልከ ዝንጉርጉር” የሚለው በዕብ. ብቻ። ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፤ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። 4ቀንበጡንም ቀነጠበ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው፤ ቅጥር ባለው#ዕብ. “በነገዶች” ይላል። ከተማም አኖረው። 5ከምድርም ዘር ወሰደ፤ በፍሬያማ እርሻም ዘራው፤ በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው። 6በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ፥ ሐረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ፥ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፤ እንዲሁ ወይን ሆነ፤ ሐረግም ሰደደ፤ ቀንበጥም አወጣ።
7“ታላቅ ክንፍና ብዙ ጽፍርም#ዕብ. “ላባም” ይላል። ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፤ እነሆም ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ ሰደደ፤ ሐረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ አዘነበለ። 8ሐረግም ያወጣ፥ ፍሬም ያፈራ፥ የከበረ ወይንም ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ፥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር። 9እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውኑ ይከናወንለት ይሆን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም። 10ተተክሎስ፥ እነሆ ይከናወንለት ይሆን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።”
የምሳሌው ትርጓሜ
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12“የሰው ልጅ ሆይ፥ ለአስቈጡኝ ለእስራኤል ቤት ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው፦ እነሆ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፤ ወደ ሀገሩም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 13ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ አማለውም፤ የምድሪቱንም ኀያላን ወሰደ፤ 14ይኸውም መንግሥቱ እንድቷረድና ከእንግዲህም ከፍ እንዳትል፥ ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ ጸንታ እንድትኖር ነው። 15እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ፤ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ ያፈረሰ ያመልጣልን?
16“እኔ ሕያው ነኝ! ያነገሠውና መሐላውን የናቀበት፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበት ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ ምሽግን በመሸጉ፥ ቅጥርንም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን በታላቅ ኀይልና በብዙ ሕዝብ በጦርነት አይረዳውም። 18ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፤ እነሆም እጁን አሳልፌ ሰጠሁ፤ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፤ ስለዚህም አያመልጥም። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝ! የናቀውን መሐላዬንና ያፈረሰውን ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ በላቸው። 20መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመድም ይያዛል፤ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ፤ በእኔም ላይ ስላደረገው ዐመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። 21ያመለጡትም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
ከእግዚአብሔር የተሰጠ ተስፋ
22“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከረዥሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹም አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረዥምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። 23ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፤ ቅርንጫፎችንም ያወጣል፤ ፍሬም ያፈራል፤ ታላቅም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፤ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል፤ ቅርንጫፉም ይሰፋል። 24የዱር ዛፎች ሁሉ፥ ረዥሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናገርሁ፤ እኔም አደረግሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ