ትንቢተ ሕዝቅኤል 13
13
በሐሰተኞች ነቢያት ላይ የተነገረ ትንቢት
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፈጽሞ ሳያዩ ከገዛ ልባቸው አንቅተው ትንቢት ለሚናገሩ ወዮላቸው! 4እስራኤል ሆይ! ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው። 5ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፤ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥርን አልሠራችሁም። 6እግዚአብሔር ሳይልካቸው፦ እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ሐሰትን ያያሉ፤ ከንቱን ያምዋርታሉ፤ ቃሉንም ማጽናት ይጀምራሉ። 7እኔም ሳልናገር፦ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ምዋርትን የተናገራችሁ፥ የሐሰት ራእይንም ያያችሁ አይደላችሁምን?”
8ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ፥ ሐሰተኛ ራእይንም ስለ አያችሁ፥ ስለዚህ እነሆ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እጄም ሐሰተኛ ራእይን በሚያዩ፥ ሕዝቤንም ለማታለል በከንቱ በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች። እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይኖሩም፤ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 10ሰላም ሳይኖር፦ ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ እነርሱ ያለገለባ ይመርጉታል፤ ይወድቃልም፤ 11ያለ ገለባም ለሚመርጉት ሰዎች፦ ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፤ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ በራሳቸው ላይ አወርዳለሁ፤ እነርሱም ይወድቃሉ፤ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል። 12እነሆ ግንቡ በወደቀ ጊዜ፦ የመረጋችሁት ምርግ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን? 13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፤ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ አወርዳለሁ። 14ያለ ገለባ የመረጋችሁትንም ቅጥር አፈርሳለሁ፤ ይወድቃል፤ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፤ መሠረቱም ይታያል፤ እርሱም ይናዳል፤ በመካከሉም ትጠፋላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 15መዓቴንም በግንቡ ላይና ያለገለባ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፤ ግንቡም ይወድቃል፤ እኔም፦ ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ። 16እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ፥ የሰላምንም ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፤ ሰላምም የለም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
በሐሰተኞች ሴቶች ነቢያት ላይ የተነገረ ተግሣጽ
17“አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ! ከልባቸው አንቅተው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ 18እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ፥ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤን ነፍስ ታጠምዳላችሁ፤ በውኑ እናንተ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ? 19ከንቱ ነገርን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ፥ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ ሕዝቤን አርክሳችኋል።
20“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፤ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፤ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ። 21ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ፤ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 22እኔም ያልመለስሁትን የጻድቁን ልብ ወደ ዐመፃ መልሳችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኀጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና፤ 23ስለዚህ፥ ሐሰትን አታዩም፤ እንግዲህም ከንቱ ምዋርትን አታምዋርቱም፤ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ