ትንቢተ ሕዝቅኤል 11
11
በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ
1መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ምሥራቅም አንጻር ወደሚያሳየው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር ወሰደኝ። እነሆም በበሩ መግቢያ ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ፤ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ። 2እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ከንቱን የሚያስቡ፥ በዚችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። 3እነርሱም፦ በውኑ ቤቶች በድንገት የሚሠሩ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። 4ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።”
5የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዬ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ቤት ሆይ! ይህን ነገር ተናግራችኋል፤ እኔም የሰውነታችሁን በደል አውቃለሁ። 6በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል፤ በጎዳናዎችዋም ሙታናችሁን ሞልታችኋል። 7ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋ ናቸው፤ ይህችም ከተማ ድስት ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። 8ሰይፍን ትፈራላችሁ፤ እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፤ በባዕዳንም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ በላያችሁም ፍርድን አደርጋለሁ። 10በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 11ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፤ እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፤ እኔም በእስራኤል ተራሮች እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።”#ምዕ. 11 ቍ. 12 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
13ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! ወዮልኝ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን?” ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
እግዚአብሔር ለስደተኞች የሰጠው ተስፋ
14የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 15“የሰው ልጅ ሆይ! በኢየሩሳሌም የሚኖሩ፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ፥ የምርኮ ሰዎችህም ሁሉ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ያልቃሉ። 16ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፤ ወደ ሀገሮችም እበትናቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ በመጡባቸው ሀገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል። 17ስለዚህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከአሕዛብ ዘንድ እቀበላቸዋለሁ፤ ከበተንሁባቸውም ሀገሮች እሰበስባቸዋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እሰጣቸዋለሁ። 18ወደዚያም ይመጣሉ፤ በደልንና ርኵሰትንም#ግእዝ “ጣዖታት” ይላል። ሁሉ ከእርስዋ ያስወግዳሉ። 19ሌላ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አሳድራለሁ፤ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ 20በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ፥ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 21ጣዖት በሚያመልኩበት ልባቸውና በኀጢአታቸው እንደ ልባቸው ቢሄዱ መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መነሣት
22ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ነበረ። 23የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማዪቱ መካከል ተነሥቶ በከተማዪቱ ምሥራቅ#“ምሥራቅ” የሚለው በዕብ. ብቻ። በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ። 24መንፈስም አነሣኝ፤ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። 25ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጣ። እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ