ኦሪት ዘፀአት 8
8
2፥ ጓጕንቸር
1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ፥ ሀገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤ 3ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፤ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ሹሞችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ቡሃቃዎችህም፥ ወደ ምድጃዎችህም ይገባሉ፤ 4ጓጕንቸሮችም በአንተ፥ በሕዝብህም፥ በሹሞችህም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።” 5እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወንድምህን አሮንን፦ ‘በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖዎቹ፥ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችንም አውጣ’ ” በለው። 6አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፤ የግብፅንም ሀገር ሸፈኑ። 7የግብፅ ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፤ በግብፅም ሀገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ።
8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔ፥ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ” አላቸው። 9ሙሴም ፈርዖንን፥ “ጓጕንቸሮቹ ከአንተ፥ ከሕዝብህም፥ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ፥ ለሹሞችህም፥ ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ ቅጠረኝ” አለው። ፈርዖንም፥ “ነገ” አለው። 10ሙሴም፥ “ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እሺ እንደ አልህ ይሁን። 11ጓጕንቸሮቹም ከአንተ፥ ከቤቶችህም፥ ከመንደሮችህም፥ ከሹሞችህም፥ ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ” አለው። 12ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም ፈርዖን እንደ ቀጠረው ሰለ ጓጕንቸሮቹ መራቅ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13እግዚአብሔርም ሙሴ እንደ አለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት፥ ከመንደርም፥ ከሜዳም ሞቱ። 14እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች። 15ፈርዖንም ጸጥታ እንደ ሆነ በአየ ጊዜ ልቡ ደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው አልሰማቸውም።
3፥ ቅማል
16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “አሮንን፦ ‘በትርህን በእጅህ ዘርጋ፤ የምድሩንም ትቢያ ምታ’ በለው፤ ቅማልም በግብፅ ሀገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ይወጣል።” 17አሮንም እጁን ዘረጋ፤ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፤ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ ሀገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። 18የግብፅ ጠንቋዮችም በአስማታቸው ቅማል ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። 19ጠንቋዮችም ፈርዖንን፥ “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።
4፥ ተናካሽ ዝንብ
20እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ማልደህ ተነሣ፤ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ፥ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በምድረ በዳ እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ፥ በአንተ፥ በሹሞችህም፥ በሕዝብህም፥ በቤቶችህም ላይ የውሻ ዝንብ እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች፥ የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በውሻ ዝንብ ይመላሉ። 22በዚያም ቀን የምድር ሁሉ አምላክ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የውሻ ዝንብ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ። 23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ነገር ነገ በምድሪቱ ላይ ይሆናል።” 24እግዚአብሔርም እንዲህ አደረገ፤ የውሻው ዝንብም በፈርዖን ቤት፥ በሹሞቹም ቤቶች ውሰጥ፥ በግብፅም ሀገር ሁሉ መጣ፤ ምድሪቱም ከውሻው ዝንብ የተነሣ ጠፋች።
25ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ በዚያች ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው። 26ሙሴም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ግብፃውያን እርም የሚሉትን እንሠዋለንና እንዲሁ ይሆን ዘንድ አይቻልም፤ እነሆ፥ ግብፃውያን እርም የሚሉትን እኛ በፊታቸው ብንሠዋ በድንጋይ ይወግሩናል። 27እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እግዚአብሔር እንዳዘዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን” አለ። 28ፈርዖንም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን በጣም ርቃችሁ አትሂዱ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩልኝ” አለ። 29ሙሴም፥ “እነሆ፥ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፤ ወደ እግዚአብሔርም እጸልያለሁ፤ የውሻ ዝንቡም ከአንተ፥ ከሹሞችህና ከሕዝብህ ነገ ይርቃል፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ሕዝቡን እንደማትለቅቅ እንደገና ማታለልን አትድገም።” 30ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 31እግዚአብሔርም ሙሴ እንደ አለ አደረገ፤ የውሻውንም ዝንብ ከፈርዖን፥ ከሹሞቹም፥ ከሕዝቡም አራቀ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ