ኦሪት ዘፀአት 38
38
የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ አሠራር
(ዘፀ. 27፥1-8)
1ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከማይነቅዝ ዕንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበረ። 2ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ሥረ-ወጥ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው። 3የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦዎቹንም፥ የእሳት ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ። 4እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያው አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው። 5ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ። 6መሎጊያዎቹንም ከማይነቅዝ ዕንጨት ሠራ፤ በናስም ለበጣቸው። 7ይሸከሙባቸውም ዘንድ በመሠዊያው ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቃዎቹም ሠርቶ ክፍት አደረገው።
የመታጠቢያው ሰን አሠራር
(ዘፀ. 30፥18)
8የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ።#በብራናው የግእዝ መጽሐፍ ምዕ. 38 ቍ. 7 እና 8 ይረዝማል።
የቤተ እግዚአብሔር ዐደባባይ
(ዘፀ. 27፥9-19)
9ለድንኳኑም በደቡብ በኩል በስተቀኝ አደባባይ አደረገ፤ የአደባባዩ መጋረጃም ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠራ ርዝመቱ መቶ ክንድ ነበረ። 10ሃያውንም ምሰሶዎቻቸውንና ሃያውን እግሮቻቸውን ከናስ አደረገ፤ የምሰሶዎቹንም ኵላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ። 11በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጃዎች፥ ከናስም የተሠሩ ሃያ ምሰሶዎችንና ሃያ እግሮችን፥ ለምሰሶዎችም የብር ኵላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 12በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጃዎች፥ ዐሥሩንም ምሰሶዎች፥ ዐሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶዎቹም የብር ኵላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 13በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጃዎችን አደረገ። 14በአዜብ በኩል የመጋረጃዎች ርዝመት ዐሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶዎቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ። 15እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ ዐሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች፥ ሦስትም ምሰሶዎች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ። 16በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጃዎች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር። 17የምሰሶዎቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶዎቹም ኵላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶዎቹም ጕልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው። 18የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሃያ ክንድ ነበረ፤ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች አምስት ክንድ ነበረ፤ 19ከናስ የተሠሩ ምሰሶዎቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኵላቦቹም የብር ነበሩ፤ ጕልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር። 20የድንኳኑም ካስማዎች፥ በዙሪያውም ያሉ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ።
ለድንኳኑ ሥራ የተሰጠው ወርቅና ብር
21በካህኑ በአሮን ልጅ በይታምር እጅ የሌዋውያን ተልእኮ ይሆን ዘንድ ሙሴ ከእግዚአብሔር እንደታዘዘ የምስክሩ ድንኳን ሥርዐት ይህ ነው። 22ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። 23ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሒሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም በሰማያዊ፥ በሐምራዊ፥ በቀይም ግምጃ፥ በጥሩ በፍታ የሽመና ሥራ ይሠራ ዘንድ የቅርጽ፥ የሽመናና የጥልፍ ሥራ አለቃ ነበረ።
24የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ ለድንኳኑ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሃያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠሳሳ ሰቅል ነበረ። 25በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ። 26እያንዳንዱም ሰው አንድ አንድ ዲድርክም አዋጣ፤ አንድ ዲድርክም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን የሰቅል ግማሽ ነው፤ ይህም የተዋጣው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ከተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበረ። 27መቶውም የብር መክሊት ለድንኳኑ ምሰሶዎች እግሮችና ለመጋረጃው ምሰሶዎች እግሮች ተደረገ፤ መቶውም መክሊት ለመቶ እግሮች፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ሆነ። 28ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶዎቹን ኵላቦችና ዘንጎች አደረገ፤ የምሰሶዎቹንም ጕልላቶች ለበጠ። 29የተሰጠውም ናስ አራት መቶ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 30ከእርሱም የምስክሩን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ 31በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የድንኳኑንም ካስማዎች ሁሉ፥ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 38: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ