ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አደገ፤ ወደ ወንድሞቹም ወጣ፤ መከራቸውንም ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው ከወንድሞቹ ከእስራኤል ልጆች አንዱን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያ ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለው፤ በአሸዋ ውስጥም ቀበረው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ ሙሴም በዳዩን፥ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። ወንድሙን የሚበድለው ያም ሰው፥ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን ትናንት እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፥ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአልን?” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴንም ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ ወደ ምድያም ምድር በደረሰ ጊዜም በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ። ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የአባታቸውንም የዮቶርን በጎች ይጠብቁ ነበር፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም የዮቶርን በጎች ሊያጠጡ የውኃዉን ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ አዳናቸው፤ እየቀዳም በጎቻቸዉን አጠጣላቸው። ወደ አባታቸውም ወደ ራጉኤል መጡ እርሱም፥ “ዛሬስ እንዴት ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣልን” አሉት። ልጆቹንም፥ “ሰውዬው ወዴት ነው? ለምንስ ያን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት፤ እንጀራም ይብላ” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። ያችም ሴት ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ሙሴም፥ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። ዳግመኛም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ኤልኤዜር አለው፤ የአባቴ ፈጣሪ ረዳቴ ነው ሲል። ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ዐሰበ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች ጐበኛቸው፤ ታወቀላቸውም።
ኦሪት ዘፀአት 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 2:11-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች