ኦሪት ዘጸአት 2:11-25

ኦሪት ዘጸአት 2:11-25 አማ54

በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፤ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለ፤ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። ያም፦ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ዐረፈ። ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውንም ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ፦ “ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣ፤” አሉ። ልጆቹንም፦ “እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት፤ እንጀራም ይብላ፤” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች፤ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}